በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ የተከናወነው የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ያለፉትን ቀናት በግብፅ ከተከናወነ በኋላ ከደቂቃዎች በፊት ፍፃሜውን አግኝቷል። የክፍለ አህጉሩ የሊግ አሸናፊ ክለቦች በስድስት ቀጠና ተከፋፍለው ባደረጉት ማጣሪያ የተለዩትን ክለቦች ከውድድሩ አስተናጋጅ ሀገር ክለብ ጋር በማካተት ሲከናወን የነበረው ውድድር ዛሬ ምሽት የደቡብ አፍሪካውን ማሜሉዲ ሰንዳውንስ እና የጋናው ሀሳካስ ሌዲስ ባደረጉት የፍፃሜ ጨዋታ ተቋጭቷል።
ኢትዮጵያዊቷ እንስት ዳኛ ሊዲያ ታፈሠ ከናይጄሪያ፣ ሞሪታኒያ እና ግብፅ ረዳቶቿ ጋር በመሆን የመራችው ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር የተደረገበት ሲሆን የደቡብ አፍሪካውን ማሜሉዲ ሰንዳውንስንም በቹኔ ሞርፌ እና አንዲውሲ ማጎኪ ጎሎች 2-0 አሸናፊ አድርጓል።
ሰንዳውንስ ድሉን ተከትሎ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገውን የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ከፍ ያደረገ ክለብ ሆኗል። በ2016 የወንዶች ቻምፒዮንስ ሊግ ያነሳው ክለቡ ከአምስት ዓመታት በኋላ በሴቶች ዘርፍ በመድገምም ባለ ታሪክ ሆኗል።
የሰንዳውሷ አንዲሌ ድላሚኒ የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆና ስትመረጥ የሀሳካሷ ኤቬሊይን ባዱ የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ እና ኮከብ ተጫዋች ሆና አጠናቃለች።