የአዲስ አበባ ከተማ የአሠልጣኝነት ጉዳይ?

በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያሳደገውን አሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር ከሜዳ ውጪ በተፈጠረ የዲሲፕሊን ጉዳይ ያሰናበተው የዋና ከተማው ክለብ አዲስ አበባ ከተማ በጊዜያዊ አሠልጣኙ ደምሰው ፍቃዱ እየተመራ ሁለት ጨዋታዎችን (ከአርባምንጭ ከተማ እና ከመከላከያ) አከናውኖ ሽንፈት እና ድል ማስመዝገቡ ይታወሳል። በቅርቡ ፍሰሐ አገኘውን የቴክኒክ ዳይሬክተር አድርጎ የቀጠረው ክለቡም ዋና አሠልጣኝ ይቀጥራል ወይስ? የሚለው ጉዳይ ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን የቦርድ አባላቶቹ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ተረድታለች።

የክለቡ ቦርድ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ደግሞ የመጨረሻዎቹን ሁለት ጨዋታዎች በጊዜያዊነት የመሩት አሠልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ አሁንም በጊዜያዊነት የሚዘልቁ ይሆናል። ምናልባት አሠልጣኙ በቀጣዮቹ ሦስት ጨዋታዎች የሚያመጡትን ውጤት ተንተርሶ ግን ቀጣይ ውሳኔዎች እንደሚወሰኑ አውቀናል። በእነዚህ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አዲሱ የቴክኒክ ኃላፊ ፍሰሐ ለቡድኑ ቀርበው እርዳታ እንዲያደርጉ እንደሚደረግ ሰምተናል።

አዲስ አበባ ከተማ በአራተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የወቅቱን የሊጉን አሸናፊ ፋሲል ከነማን ሠኞ 9 ሰዓት የሚገጥም ይሆናል።