የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ለ20 ቀናት ከተቋረጠ በኋላ በነገው ዕለት የአራተኛ ሳምንት መርሐ-ግብሮችን በማድረግ ይቀጥላል። የዚህ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ የሆነው የአርባምንጭ ከተማ እና የባህር ዳር ከተማን ጨዋታም እንደሚከተለው በቅድመ ዳሰሳችን ተመልክተነዋል።
በሦስቱ የሊግ ጨዋታዎች በእግርኳስ የሚከሰቱትን ድል ሽንፈት እና ነጥብ መጋራት ተራ በተራ ያስተናገዱት አርባምንጭ ከተማዎች በወረቀት ላይ የዋንጫ ተፎካካሪ የሆነውን ባህር ዳር ከተማ በመርታት ካሉበት ስምንተኛ ደረጃ መስፈንጠርን እያለሙ ጨዋታውን እንደሚቀርቡ ይገመታል።
በአሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመራው አዲሱ የሊጉ ክለብ አርባምንጭ በእስካሁኖቹ ሦስት ጨዋታዎች ቀጥተኛ አጨዋወትን በመከተል ሲጫወት ታይቷል። እርግጥ ቡድናዊ መዋቅር ባለው የማጥቃት እና የመከላከል ቅርፅ ውስጥ ተጫዋቾቹ ተገርተው በአንድነት ሲጫወቱ መታየቱ መልካም ቢሆንም አዘውትረው ሲጠቀሙት የሚስተዋለው የረጃጅም ኳሶች አጨዋወት ግን ተገማች እያደረጋቸው ይገኛል። በሦስቱ ጨዋታዎች እንደታየው እንዳይሆን ደግሞ አሠልጣኝ መሳይ ከነገው ጨዋታ በፊት የ20 ቀናት ጊዜ ስላገኙ ክፍተቱን አሻሽለው እንደሚመጡ ይታሰባል።
በአመዛኙ አካላዊ አጨዋወት ሲከተሉ የሚታየው አዞዎቹ ከከፍተኛ ሊግ አጨዋወታቸው የወረሱት ባህሪ ነገም እንደሚቀጥል ይታወቃል። በተለይ ከአካላዊ አጨዋወታቸው በተጨማሪ የታጋይነት ባህሪ በጉልህ ይስተዋልባቸዋል። የነገ ተጋጣሚያቸው ባህር ዳር ከተማ ደግሞ በአንዳንድ የጨዋታ ቅፅበቶች የሚስተዋልበት የትኩረት ማነስ ክፍተትን በመንተራስ ቅፅበታዊ ምላሽ የሚሰጡ ከሆነ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።
አብነት ተሾመ እና ሱራፌል ዳንኤል ጉዳት ላይ በመገኘታቸው ምክንያት በነገው ጨዋታ ቡድናቸውን አያገለግሉም። ከሁለቱ ተጫዋቾች ውጪ ግን ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና በስብስቡ በኩል የለም።
በሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ በመሪው ፋሲል ከነማ በሁለት ነጥቦች ተበልጠው ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህር ዳር ከተማዎች ዓመቱን በተከታታይ ድል ጀምረው በሦስተኛ ሳምንት አቻ የወጡበትን ውጤት ዳግም በማሻሻል በዋንጫ ተፎካካሪነቱ ለመዝለቅ ድልን እያሰቡ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታሰባል።
የሊጉን የመጀመሪያ ጨዋታ በአራት ከዛ ደግሞ በሦስት ተከላካዮች ሲጫወት የታየው ባህር ዳር በየመጫወቻ ቦታው ያለውን የተትረፈረፈ የተጫዋቾች ምርጫ ለአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጥሩ የራስ ምታት የሆናቸው ይመስላል። በተለይ በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች ወሳኞቹ ተጫዋቾች በማይኖሩበት ጊዜ በተለየ የጨዋታ መንገድ እና የተጫዋች አደራደር ቅርፅ ቡድናቸውን እየቃኙ ወደ ሜዳ ሲገቡ ተስተውሏል። ይህ ደግሞ ቡድኑ በተጫዋችም ሆነ በአጨዋወት ረገድ እንዳይገመት ያደርገዋል።
ከሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች አንዱ የሆነው ኦሲ ማውሊ በነገው ጨዋታ የአርባምጭ የራስ ምታት የባህር ዳር ደግሞ መተማመኛ እንደሚሆን ይገመታል። በአየር እና በመሬት ላይ ኳስ አጠቃቀሙ ጥሩ የሆነው ማውሊ ቦታዎችን ቶሎ ቶሎ ከሚቀያየሩት የአጥቂ አማካዮቹ እና የመስመር ተከላካዮቹ የሚደርሰውን ኳስ እንዳይጠቀም የአርባምንጭ ተከላካዮች በተቀናጀ መልኩ መከላለል ይጠበቅባቸዋል። በባህር ዳር በኩል ግን በመጨረሻው የወልቂጤ ጨዋታ ላይ የታየው ፍጥነት የሌለው የማጥቃት እንቅስቃሴ እና ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚደረግ ሽግግር የሚኖረው የመስመሮች ክፍተት ትኩረት የሚፈልግ ነው። በተለይ የመስመር ተከላካዮቹ አጥቅተው ሲመለሱ የሚኖራቸው የኋልዮሽ ሩጫዎች ፍጥነት ዝግ ማለት የተጋጣሚ አጥቂዎች በቦታው ክፍተት እንዲያገኙ ያረጋቸዋል።
በሞገዶቹ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር የትከሻ ጉዳት ያስተናገደው ኤርትራዊው አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን ከጉዳቱ አገግሞ ልምምድ መስራት በመጀመሩ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል። እንደ ዓሊ ጉዳት ላይ የነበሩት ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ተመስገን ደረሰ ግን ባለማገገማቸው ከነገው ፍልሚያ ውጪ ናቸው።
ይህንን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ በአልቢትርነት እንደሚመሩት ታውቋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)
ሳምሶን አሰፋ
ወርቅይታደስ አበበ – በርናንድ ኦቺንግ – አንድነት አዳነ – ተካልኝ ደጀኔ
ሀቢብ ከማል – እንዳልካቸው መስፍን – አንዱዓለም አስናቀ – ፀጋዬ አበራ
በላይ ገዛኸኝ – ኤሪክ ካፓይቶ
ባህር ዳር ከተማ (4-1-3-2)
አቡበከር ኑሪ
አህመድ ረሺድ – ሰለሞን ወዴሳ – ፈቱዲን ጀማል – ግርማ ዲሳሳ
አለልኝ አዘነ
ፉዓድ ፈረጃ – ፍፁም ዓለሙ – አብዱልከሪም ንኪማ
ዓሊ ሱሌይማን – ኦሴ ማውሊ