በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በኦሮሚያ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስተባባሪነት ከኅዳር 1 ጀምሮ በአዳማ ከተማ ለሠላሳ ሰልጣኞች ሲሰጥ የነበረው የ ዲ ላይሰንስ የአሰልጣኞች ስልጠና በዛሬው ዕለት ተጠናቋል፡፡
ሁለቱ እንስት ኢንስትራክተሮች ሰላም ዘርአይ እና በኃይሏ ዘለቀ እንዲሁን በካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ አማካኝነት ሲሰጥ የነበረው ይህ ስልጠና የተግባር እና የክፍል ስልጠናን በንድፈ ሀሳብ አዝሎ ሲሰጥ የነበረ ሲሆን ካፍ በድጋሚ ሀገራት ላይሰንስ እንዲሰጡ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በዚህ ዓመት ስልጠናው ሲደረግ አራተኛው ሆኗል፡፡
ላለፉት ቀናት የቀድሞው ተጫዋቾች ፣ የፕሮጀክት አሰልጣኞች እና ወደ ስልጠናው አለም ለመግባት ፍላጎት ያላቸው አሰልጣኞችን ለማብቃት ሲሰጥ የነበረው ይህ ስልጠና በዛሬው ዕለት ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው፣ ስልጠናውን ሲሰጡ የሰነበቱት ኢንስትራክተር ሰላም ዘርዓይ እና በኃይሏ ዘለቀ፣ አቶ ደረሰ፣ የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ ጨምሮ አቶ ከድር እንዳልካቸው የኦሮሚያ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ ፣ አቶ ፍሮምሳ ለገሰ የክልሉ እግር ኳስ ፌድሬሽን የፅህፈት ቤት ኃላፊ በመዝጊያው ዕለት ተገኝተዋል፡፡ በስልጠናው ተሳታፊ ለነበሩ ሁሉም ሰልጣኞች የተዘጋጀላቸውን ሰርተፍኬት የተቀበሉ ሲሆን በመጨረሻም ለዚህ ስልጠና መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉት የፌዴሬሽኑ አመራሮች እና ስልጠናውን ለሰጡ አካላት የኦሮሚያ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የማስታወሻ ስጦታ አበርክተዋል፡፡