ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

የነገ ምሽቱን ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንደሚከተለው ተመልክተናል።

ቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለቀናት ከመቋረጡ ቀደም ብሎ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች የተራራቁ ውጤቶችን ያስመዘገቡት ወልቂጤ እና ሀዋሳ ነገ አራተኛ ግጥሚያቸውን እርስ በእርስ ያደርጋሉ። እስካሁን ከድል ጋር ያልተገናኙት ወልቂጤዎች ሁለት የአቻ ውጤቶችን አስመዝግበው በሰንጠረዡ የመጨረሻ ክፍል ላይ የተቀመጡ ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው ሁለት ድሎችን አሳክተው ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ወልቂጤ ከተማ እንደአምናው ሁሉ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ከተፎካካሪዎቹ ጋር ሲነፃፀር ደካማ የሚባል ቡድን አልነበረም። ሦስቱ ጨዋታዎች ግን በተለይም በማጥቃት አማራጬቹ እና ውህደቱ ላይ መሻሻል እንደሚያስፈልገው የጠቆሙ ነበሩ። አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውም ከሦስተኛው የባህር ዳር ጨዋታ በኋላ ”ከበድኑ ብዙ ጠብቁ” ሲሉ መደመጣቸው በሂደት ችግሮቹን የመቅረፍ ብቃቱ እንዳለው በፅኑ እንደሚያምኑ የሚጠቁም ነበር። ከቡድኑ ደካማ አጀማመር አንፃርም ያለፉት የዕረፍት ቀናት ያለበቂ የዝግጅት ጨዋታዎች ወደ ውድድር የገባውን ቡድን አስተካክሎ ለመመለስ ጥሩ አጋጣሚ የፈጠሩ ይመስላሉ።

የዕረፍት ቀናቱ ለሀዋሳ ከተማ ከዚህ የተለየ እንድምታ ያላቸው ይመስላል። ሀዋሳ አሁን ካለበት ደረጃ ባለፈ በሦስተኛው ሳምንት የሮድዋ ደርቢን በጥሩ ብቃት እና ድል መወጣቱ ሲታሰብ በዛው ስሜት ውስጥ ቀጣይ ጨዋታዎችን መከወን ተጠቃሚ ሊያደርገው ይችል እንደነበር ያስገምታል። የነገው ጨዋታ ውጤቱን አብዝቶ ከሚፈልገው ቡድን ጋር የሚያደርግ መሆኑ በራሱ በቀዳሚዎቹ ሳምንታት ውጤት ላይ የተመሰረተ ከፍ ያለ በራስ መተማመን ይዞ ወደ ሜዳ እንዲገባ ይጠበቅበታል።

የኳስ ቁጥጥር ብልጫን መሰረት ያደረገ አቀራረብ ያለው ወልቂጤ ከተማ በቁጥር የበረከቱ ባይሆኑም የግብ ዕድሎችን ሲፈጥር ይታያል። ዕድሎችን የመጨረስ ችግር ያለበት ቡድኑ በመስመር አጥቂነት እስካሁን ያሉትን አማራጮች በተለያየ አኳኋን በመቀያየር እየተጠቀመ ይገኛል። የፊት መስመር ተሰላፊነቱን ግን በዋናነት ለጌታነህ ከበደ ሰጥቷል። ከባህር ዳር ነጥብ የተጋራባትን ግብም ከጌታነህ ማግኘቱ አይዘነጋም። ከዚህ አንፃር የነገውን ጨዋታ ስናስበው የጌታነህ በብሔራዊ ቡድን ግዳጅ ላይ መሰንበት ከሚያስከትለው የጨዋታ እና ጉዞ ድካም አንፃር ሰራተኞቹ ከፊት ይበልጥ ሳስተው እንዳይታዩ ያሰጋል።

የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ቡድን በሲዳማው ጨዋታ ጥሩ አፈፃፀም አሳይቷል። ኳስ ይዞ ለመጫወት ከሚመሞክር ተጋጣሚ ጋር ደግሞ ምን ዓይነት አቀራረብ እንደሚኖረው የነገው ጨዋታ እንደሚያስመለክተን ይጠበቃል። ከሁሉም በላይ በሲዳማው ጨዋታ ለተጋጣሚ ጠንካራ ጎን ምላሽ ከመስጠት አንፃር የታየበት ጠንካራ ጎን ለነገ ግብዐት የሚሆነው ነው። እንደአስፈላጊነቱ ኃይል የቀላቀለ አጨዋወትን መተግበር ፣ የፊት መስመር ተሰላፊዎችን ያካተተ ጥሩ የመከላከል ሽግግር እና ተጋጣሚ በራሱ ሜዳ ላይ ስህተቶችን እንዲሰራ ማድረግ ለሀዋሳ ከተማ ከሦስተኛ ሳምንት ለነገው ጨዋታ የሚወሰዱ ነጥቦች ይመስላሉ።

 

በነገው ጨዋታ የወልቂጤ ከተማዎቹ ዮናስ በርታ እና አቡበከር ሳኒ አሁንም ከጉዳታቻው ያላገገሙ ሲሆን ዮናታን ፍሰሀም በቡድኑ የጉዳት ዝርዝር ውስጥ የተካተተ ተጫዋች ሆኗል። በሀዋሳ ከተማ በኩል ግን የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና አልተሰማም።

ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ ተካልኝ ለማ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በ2013 የውድድር ዓመት ሁለቱን ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ያገናኙት ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ያለግብ የተጠናቀቁ ነበሩ።

 

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ስልቪያን ግቦሆ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ

አህመድ ሁሴንሎ – ጌታነህ ከበደ – ጫላ ተሺታ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

መሀመድ ሙንታሪ

ዳንኤል ደርቤ – ላውረንስ ላርቴ – ፀጋሰው ድማሙ – ዮሃንስ ሱጌቦ

ወንድማገኝ ኃይሉ – አቡዱልባሲጥ ከማል – በቃሉ ገነነ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ