ሪፖርት | አዞዎቹ ከመመራት ተነስተው ጣፋጭ ድል የጣናው ሞገዶቹ ላይ አስመዝግበዋል

የንባብ ቆይታ:2 ደቂቃ, 45 ሰከንድ

አርባምንጭ ከተማዎች በሦስተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር አንድ አቻ ከተለያዩበት ፍልሚያ አንድነት አዳነን ብቻ በአሸናፊ ፊዳ ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ ባህር ዳር ከተማዎች ደግሞ በግብ ብረቶቹ መሐከል ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ያደረገው ፋሲል ገብረሚካኤልን በአቡበከር ኑሪ፣ ተከላካዩ አህመድ ረሺድን በመሳይ አገኘው፣ የአጥቂ አማካዩን ፎዐድ ፈረጃን በሳላምላክ ተገኘ እንዲሁም ሌላኛውን ተከላካይ መናፍ ዐወልን በዜናው ፈረደ ለውጠው ጨዋታውን ቀርበዋል።

ጨዋታውን በጥሩ ተነሳሽነት የጀመሩ የሚመስሉት አርባምንጭ ከተማዎች የሚያገኟቸውን ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመላክ እንዲሁም ባህር ዳሮች ኳስ ከግብ ክልላቸው ሲጀምሩ ተጭነው ለመቀበል በመሞከር ቀዳሚ ለመሆን ሲጥሩ ታይቷል። ይህ ቢሆንም ግን ኳስን ተቆጣጥረው በትዕግስት ለመጫወት የሚሞክሩት ባህር ዳር ከተማዎች ነበሩ የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት። በዚህም ኦኪ ማውሊ ከርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት በግራ እግሩ አክርሮ የመታው ኳስ የግብ ዘቡ ሳምሶን ይዞታል። ለዚህ ሙከራ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያሰቡት አርባምንጮች ከደቂቃ በኋላ ሀቢብ ከማል ከርቀት በመታው ኳስ የባህር ዳርን ግብ ፈትሸው ተመልሰዋል።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው እየገቡ የሚመስሉት ባህር ዳሮች በግራ መስመር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል አምርተው በአብዱልከሪም ንኪማ አማካኝነት ጥቃት ሰንዝረው ነበር። ከወትሮ በተለየ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ላይ ፍጥነት ጨምረው የቀረቡት አዞዎቹ በ12ኛው ደቂቃ በላይ ገዛኸኝ በተከላካዮች መሐል የተሰነጠቀለትን ኳስ ለመጠቀም በጣረው ኳስ ቀዳሚ ሊሆኑ ነበር። ጨዋታው 21ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን ባህር ዳር ከተማዎች በአምበላቸው አማካኝነት ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። የግል ብቃቱን ያሳየበትን ኳስ ከሳላምላክ የተቀበለው ፍፁም ዓለሙ የአርባምንጩን ተከላካይ በማለፍ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

ግቡ ከተቆጠረ በኋላ ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ማስመልከት የቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እስከ 41 ደቂቃ ድረስ የጠራ የግብ ሙከራ አልተስተናገደበትም። አርባምንጭ ከተማዎች ግን በደቂቃዎቹ በቶሎ ወደ አቻነት ለመምጣት በበላይ እና በሀቢብ አማካኝነት በተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርጉ ተስተውሏል። ከላይ እንደተጠቀሰው በ41ኛው ደቂቃ ግን የመዓዘን ምትን መነሻ ያደረገ ኳስ ዜናው ፈረደ አግኝቶ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሯል። በቀጣዩ ደቂቃ ግብ የሚያስቆጥር የሚመስለው አርባምንጭ አጋማሹ ሊገባደድ ሲል በሰከንዶች ልዩነት በሀቢብ እና በላይ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን አድርጎ በግብ ጠባቂ መክኖባቸዋል። ሙሉ የአጋማሹ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩት 2 ደቂቃዎች አጋማሽ ላይ የባህር ዳሩ የግብ ዘብ አቡበከር ኳስ ከእጁ አውርዶ ሲመታ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሉን አልፏል በሚል የተሰጠውን የቅጣት ምት ሀቢብ ከማል በጥሩ ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎት ቡድኑን አቻ አድርጓል።

በታጋይነታቸው የሁለተኛውንም አጋማሽ የጀመሩት የአሠልጣኝ መሳይ ተጫዋቾች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በድፍረት በማጥቃት ሲጫወቱ ነበር። በተለይ ኬኒያዊው አጥቂ ኤሪክ ካፓይቶ ከአንድም ሁለት ጊዜ ሳጥን ውስጥ ተገኝቶ በእግሩ እና በግንባሩ ግብ ለማስቆጠር ዳድቶ ነበር። ከካፓይቶ ኳሶች በተጨማሪ የግቡ ባለቤት ሀቢብ በ61ኛው ደቂቃ ወደ ግራ ባዘነበለ የፍፁም ቅጣት ምቱ ክፍል ያገኘውን ኳስ ሁለተኛ ግብ ሊያረገው ነበር።

ከባድ ፈተና በሜዳ ላይ የገጠማቸው ባህር ዳሮች ባልተረጋጋ መንገድ መጫወታቸውን ቀጥለው ሌላ ሙከራ በ65ኛው ደቂቃ አስተናግደዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም የጣናው ሞገዶቹ የራስ ምታት ሆኖ የታየው ሀቢብ የለመደ የግራ እግሩን በመጠቀም እጅግ የሰላ ኳስ ሊያስቆጥርባቸው ነበር። የቡድኑ አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱም በሦስቱም የሜዳ ክፍሎች የተጫዋች ለውጦችን ቢያደርጉም እስከ 75 ደቂቃ ድረስ ሳምሶን አሰፋን የፈተነ ጥቃት መሰንዘር አቅቷቸዋል።

ጨዋታው ቀጥሎ 75ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ባህር ዳር የአጋማሹን የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ጥቃት ሰንዝሯል። በዚህም ኦሲ ማውሊ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ለመጠቀም ሲጥር የነበረውን ኳስ ፍፁም አግኝቶት ወደ ግብ መትቶት ነበር። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በጨዋታው ብልጫ የነበራቸው አዞዎቹ ወደ ባህር ዳር ሳጥን ደርሰው በአጥቂያቸው ካፓይቶ አማካኝነት ሙከራ ሲያደርጉ ጥፋት ተሰርቶ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። አህመድ ረሺድ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትም ወርቅይታደስ አበበ ወደ ግብነት ቀይሮት አርባምንጭ መሪ ሆኗል። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድ አርባምንጭ ከተማ ጨዋታውን አሸንፎ ወጥቷል።

ውጤቱን ተከትሎ በጨዋታው የተሻለ ተንቀሳቅሰው ሦስት ነጥብ ያገኙት አርባምንጭ ከተማዎች ነጥባቸውን ሰባት አድርሰው በጊዜያዊነት ከስምንተኛ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል። ከመሪነት ተነስተው ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ባህር ዳሮች ደግሞ በተመሳሳይ 7 ነጥቦች (በግብ ክፍያ በልጠው) ባሉበት ሁለተኛ ደረጃ ፀንተው ተቀምጠዋል።

ያጋሩ