ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ አሳክቷል

አሰልቺ ይዘት በነበረው እና ሁለት ቀይ ካርዶችን በተመለከትንበት የአመሻሹ ጨዋታ የአብዱልከሪም ወርቁ የ64ኛው ደቂቃ ግብ ወልቂጤ ከተማ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥብ እንዲያሳኩ አስችሏል።

በወልቂጤዎች በኩል በመጨረሻው የባህር ዳር ከተማ ጨዋታ ከተጠቀሙት የመጀመሪያ ተመራጭ ተሰላፊዎች ሦስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ሀብታሙ ሸዋለም፣ ጫላ ተሺታ እና አህመድ ሁሴን በእስራኤል እሸቱ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ እና ያሬድ ታደሰ ተክተዋል። በተቃራኒው ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ሲዳማ ቡናን ከረታው ቡድናቸው ላይ በቃሉ ገነነን በማሳረፍ በሄኖክ ድልቢ ብቻ ቀይረው ወደ ጨዋታው ቀርበዋል።

ቀዝቃዛ መልክ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይበልጥ ጥንቃቄ ላይ ያተኮረ የጨዋታ ዕቅድን ለመተግበር መሞከራቸውን ተከትሎ ሳቢ ያልነበረ አጋማሽን ለማሳለፍ ተገደናል። በሜዳው አጋማሽ የተገደበ እንቅስቃሴ በበረከተበት አጋማሽ በ39ኛው ደቂቃ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን አጋጣሚ መስፍን ታፈሰ ከቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት የሞከራት እና ሲሊቪያን ግቦሆ ያዳነበት ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ኢላማዋን የጠበቀች ሙከራ ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ መጠነኛ የመነቃቃት ምልክቶችን ባሳየው ጨዋታ በ56ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ወርቁ በረጅሙ የጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ተስፋዬ ነጋሽ ከተከላካዮች አምልጦ በመግባት የሞከረውን እና መሀመድ ሙንታሪ ያዳነበት ኳስ የአጋማሹ የመጀመሪያ ሙከራ ነበር።

አንፃራዊ የበላይነት ማሳደር የጀመሩት ወልቂጤዎች በ64ኛው ደቂቃ ላይ አማካያቸው አብዱልከሪም ወርቁ በሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች ስህተት የተገኘችውን ኳስ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገችን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኃላ በደቂቃዎች ልዮነት ሀዋሳ ከተማዎች አቻ ሊሆኑበት የሚችሉበትን አጋጣሚ ቢያገኙም ብሩክ በየነ መጠቀም ሳይችሉ ቀርቷል።

በ77ኛው ደቂቃ በመጀመሪያው አጋማሽ ባልተገባ መንገድ ቢጫ ካርድ የተመለከተው አብዱልባሲጥ ከማል አብዱልከሪም ወርቁ ላይ በሰራው አደገኛ ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ለመወገድ ተገዷል።

በ83ኛው ደቂቃ ወልቂጤ ከተማዎች ሁለተኛ ግብ ሊያስቆጥሩበት የሚችሉበትን አጋጣሚ በሀይሉ ተሻገር አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያሬድ ታደሰ ሳይጠቀምበት ቀረ እንጂ ወልቂጤዎች ሁለተኛ ግባቸውን ማስቆጠር በቻሉ ነበር።

እንደ አብዱልባሲጥ ሁሉ በ87ኛው ደቂቃ የወልቂጤ ከተማው ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ መድሀኔ ብርሃኔ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል። ከቀይ ካርዱ በኃላ በነበሩት የመጨረሻ ደቂቃዎችም ሀዋሳ ከተማዎች የአቻነቷን ግብ ፍለጋ እጅግ አስፈሪ እንቅስቃሴን ማድረግ ችለዋል። በዚህም መስፍን ታፈሰ በሁለት አጋጣሚዎች እንዲሁም በቸርነት አውሽ አደገኛ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም የወልቂጤን መረብ መድፈር ሳይችሉ በመቅረታቸው ጨዋታው በወልቂጤ የበላይነት ሊጠናቀቅ ችሏል።