በወልቂጤ ከተማ የበላይነት ከተጠናቀቀው የአመሻሹ ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።
ጳውሎስ ጌታቸው – ወልቂጤ ከተማ
ስለጨዋታው
“እንዳያችሁት ቡድኔ ከዕለት ወደ እለት ለውጥ አለው ማንም ባልጠበቀው ፎርሜሽን ነበር የገባነው በሁለት አጥቂ ለመጫወት ሞክረናል ከእነሱ ጀርባ ያሉት ተጫዋቾች የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ናቸው
ከዚህ በፊት እንደገለፅኩት አጥቅተን የመጫወት ፍላጎት አለን ያንን ነበር በዛሬው ጨዋታ ያደረግነው።”
ስለተጠቀሙት የተጫዋቾች አደራደር
“አንደኛ ጌታነህ ኳስ ስለሚችል ተጫውቶ መውጣት ይችላል። ይህንን ከአማካዮቹ ጋር ልምምድ ላይ በደንብ ሰርተናል፤ በጋራ ተጫውተው እስራኤልን ለመፈለግ ነበር። በዛሬው ጨዋታ ከጌታነህ ጎል አልነበረም የፈለግነው። ተጫውቶ እንዲወጣ ነበር ይህንንም አግኝተናል።”
ስለአብዱልከሪም ወርቁ
“አብዱልከሪም አሁን ላይ ምንም አያጠያይቅም ከዚህ በፊትም ለብሔራዊ ቡድን ተመርጦ በጉዳት ነው የተመለሰው። ገና የሚያድግ ልጅ እንደመሆኑ አፍሪካ ዋንጫ ላይ ተመርጦ እናየዋለን ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ትልቅ ተሰጥኦ ያለው ልጅ ነው። አሁን ላይ ጥሩ ብቃት ላይ ነው ያለው ወደፊትም ለክለቡም ሆነ ለሀገሩ ትልቅ ነገር ማድረግ ይችላል ብዬ የምጠብቀው ተጫዋች ነው።”
ስለድሉ ትርጉም
“ሦስት የወዳጅነት ጨዋታ አድርገን ነበር ሊጉን የጀመርነው። ያም ትንሽ ተፅዕኖ ነበረው። ከአሁን በኃላ ግን ሜዳውንም እየለመድን ስለመጣን ከዚህ በኃላ ለተመልካቹ ጥሩ ጨዋታ እናሳያለን ብዬ እጠብቃለሁ።”
ዘርዓይ መሉ – ሀዋሳ ከተማ
ስለጨዋታው
“እንቅስቃሴው መጥፎ አይባልም። ጎል አካባቢ የተወሰኑ መረጋጋቶች ይቀሩናል፤ በዚያ የተነሳ እድሎችን አምክነናል። ተቃራኒ ቡድን ይህን ተጠቅሟል ማለት ይቻላል። ሁለት አደገኛ አጋጣሚ ወጥቶብናል፤ እነሱ ግን ያገኙትን ተጠቅመዋል። እንደ ቡድን ቡድናችን ጥሩ ነው፤ ቶሎ ቶሎ ጎል ጋር እንደርሳለን። ሰውም ወጥቶብን የተሻለ ተንቀሳቅሰናል፤ የሚስተካከል ነገር ነው ይስተካከላል።
ስለ መስመር ተጫዋቾቹ እንቅስቃሴ
“ተጋጣሚያችን ይዞ የመጣው አጨዋወት በራሳቸው ሜዳ በቁጥር በዝተው መጫወት ነው። ለዛም የኛ የመስመር ተጫዋቾች ብዙ ጎልበት ያወጡ ነበር። ለዚህም ነበር ተከላካዮች እየቀነስን አጥቂ ያስገባነው። ዞሮ ዞሮ ብልጫ ብንወስድም በጎል ማጀብ አልቻልንም። ያም ቢሆን ግን የመስመር ተጫዋቾቻችን ጎል ጋር ይደርሱ ነበር።”