ቅድመ ዳሰሳ | አዲስ አበባ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

የአራተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ የሆነውና በፌዴራል ዳኛ ተከተል ተሾመ የሚመራው የአዲስ አበባ እና ፋሲል ፍልሚያን እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

አዲሱ የሊጉ ክለብ አዲስ አበባ ከተማ በሦስቱ የሊጉ ጨዋታዎች ስሙ ሜዳ ላይ ባለ ብቃቱ ከመነሳቱ በላይ ከሜዳ ውጪ ባሉ ነገሮች መነሳቱ ጎልቶ ነበር። ይህ ቢሆንም በሦስተኛ ሳምንት አብሮት ያደገውን ክለብ (መከላከያ) ያሸነፈበትን ውጤት በመድገም ደረጃውን ለማሻሻል ተግቶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታሰባል።

ዋና አሠልጣኙ እስማኤል አቡበከርን ከማሰናበቱ በፊት በምክትል አሠልጣኙ ደምሰው ፍቃዱ እየተመራ ሁለት ጨዋታዎችን ያደረገው ክለቡ ዋና አሠልጣኙን ካሰናበተ በኋላ አሁንም በጊዜያዊ አሠልጣኙ እንደሚዘልቅ ተሰምቷል። ገና በጊዜ የዋና አሠልጣኝ ቦታ ላይ መረጋጋት አለመኖሩ ቡድኑን የሚጎዳው ቢመስልም በመጨረሻው የመከላከያ ጨዋታ የታየው እንቅስቃሴ ግን የሚያስገርም ነበር። በተለይ ቡድናዊ አጨዋወት፣ ተነሳሽነት፣ ታጋይነት እና አልሸነፍ ባይነት የታየበት ቡድኑ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች በነበረው የ18 ቀናት እረፍት ተቀዛቅዞ ካልመጣ ነገ ለዐፄዎቹ ፈተና ነው።

ከጅማ በመቀጠል ከሀዲያ ሆሳዕና እኩል የሊጉ ደካማ የመከላከል ክፍል ያለው አዲስ አበባ ቅንጅት የሚፈልገው የኋላ መስመሩ ላይ በሦስቱ ጨዋታዎች መረጋጋት አልታየም። እርግጥ በሦስተኛው ጨዋታ በአንፃሩ ቢሻሻልም የተጫዋች እና የመዋቅር ለውጦችን አሁንም ሲደረግበት ይታያል። ይህ ደግሞ ወሳኙ ክፍል የተረጋጋ እንዳይሆን ያደርገዋል። ከዚህ ውጪ ከወገብ በላይ ያሉት ተጫዋቾች ፍጥነት እና ቀጥተኝነት ቡድኑ አንዳች ነገር ከጨዋታው እንዲጠብቅ ያደርገዋል።

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ክለብ የሆነው ፋሲል ከነማ ዋንጫውን የግሉ አድርጎም ቢሆን ዓምና ካቆመበት የቀጠለ ይመስላል። በተለይ በሦስቱ ጨዋታዎች እንደ አዲስ የታየበት የዋንጫ ርሀብ ፍልሚያዎቹን በተሻለ የፍላጎት ደረጃ እንዲቀርባቸው ሲያደርግ ስለታየ ነገም ትልቅ የማሸነፍ ግምት ተሰጥቶታል።

በአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚመራው ፋሲል ያለፉትን ዓመታት በተረጋጋ እና ብዙ በማይነካካ ቡድናዊ መዋቅር የውድድር ዓመቱን ሲጀምር ይታያል። ይህ ነገር ደግሞ ዘንድሮም ተደግሟል። በርከት ያሉ ተጫዋቾች የማይወጡበት እና የማይገቡበት መሆኑ ደግሞ በዓመት መጀመሪያ ላይ በሌሎች ክለቦች የሚስተዋለው ያለመናበብ እና ያለመቀናጀት ችግር እንዳይታይበት አድርጓል። ይህ እንደጠቀመው በጉልህ በሚታይ መልኩም በሦስቱ ጨዋታዎች (በሁለተኛው የወልቂጤ ጨዋታ በአንፃሩ ቢፈተንም) እምብዛም ሳይቸገር ሲጫወት ነበር። በተለይ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ያለው ጥንካሬን ሊያጠፋ የሚችል የጨዋታ ዕቅድ አዲስ አበባዎች ወደ ሜዳ ይዘው የማይገቡ ከሆን ከፍተኛ ፈተና ሊደቀንባቸው ይችላል።

በእስካሁኖቹ ጨዋታዎች የሊጉ መሪ የሆነው ፋሲል የሊጉም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ (8) ክለብ ነው። እነዚህ ግቦች ደግሞ በአጥቂ መስመር ተጫዋቾቹ ብቻ ጥገኛ በመሆን የተቆጠሩ አለመሆናቸው እና በአማካይም ሆነ በተከላካይ ክፍሉ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ያስቆጠሯቸው መሆኑን ስናስታውስ የቡድኑ የግብ ማስቆጠሪያ መንገድ የተገደበ አለመሆኑን እንረዳለን። ይህ ደግሞ ተጋጣሚ ቡድን ግብ እንዳይቆጠርበት በሚያደርገው ጥረት ላይ ከፍተኛ ችግር የሚያመጣ ነው። የሆነው ሆኖ ብዙም እንከኖች የሌሉበት የሚመስለው ክለቡ በሦስቱ ጨዋታዎች ያታየበትን ጨዋታን የማሸነፍ ረሀብ ነገም የማስቀጠል ሀላፊነት አሠልጣኝ ሥዩም ላይ ተጥሎ ጨዋታውን ይቀርባሉ።

በፋሲል በኩል አጥቂው ኦኪኪ አፎላቢ እና የአጥቂ አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸው ጉዳት ላይ በመሆናቸው ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– የሁለቱ ቡድኖች ብቸኛ የእርስበርስ ግንኙነት በ2009 የተደረገ ሲሆን የመጀመርያውን ዙር ፋሲል ከነማ 2-0፣ የሁለተኛውን ዙር አዲስ አበባ ከተማ 1-0 አሸንፈዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል ተሾመ

ልመንህ ታደሰ – አሰጋኸኝ ጽጥሮስ – ኢያሱ ለገሰ – ያሬድ ሀሰን

ብዙዓየሁ ሰይፉ – ሙለቀን አዲሱ – ቻርለስ ሪባኑ

ሳዲቅ ተማም – ፍፁም ጥላሁን – ሪችሞንድ አዶንጎ

ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)

ሚኬል ሳማኬ

አብዱልከሪም መሐመድ – ያሬድ ባየህ – አስቻለው ታመነ – አምሳሉ ጥላሁን

ከድር ኩሊባሊ – ሀብታሙ ተከስተ

ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – በረከት ደስታ

ፍቃዱ ዓለሙ