የሁለተኛው የጨዋታ ቀን መዝጊያ የሆነውን ግጥሚያ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።
በወጣት አሰልጣኞች የሚመሩት ሀዲያ ሆሳዕና እና አዳማ ከተማ ነገ ምሽት በአራተኛ ሳምንት ጨዋታ ይገናኛሉ። የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረቱ ሆሳዕና እስካሁን ድል ሳይቀናው በአንድ ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የጨዋታው ውጤት በእጅጉ ያስፈልገዋል። በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ስር የሚሰለጥነው አዳማ ከተማም ከተጋጣሚው በተሻለ አራት ነጥቦች ይሰብስብ እንጂ ከወገብ በታች የተቀመጠ በመሆኑ ደረጃውን ለማሻሻል የዓመቱን ሁለተኛ ድል ማስመዝገብ ይኖርበታል።
ሁለቱ ተጋጣሚዎች በሦስተኛው ሳምንት ጠንከር ያለ መከላከልን በተገበሩ ቡድኖች ተፈትነው ተመልክተናቸዋል። አዳማ በወላይታ ድቻ የተሸነፈበት ሆሳዕናም ከአርባምንጭ ነጥብ የተጋራባቸው ጨዋታዎች ከኳስ ጀርባ መቆየትን እና በመልሶ ማጥቃት የመውጣት ዕቅድ ካላቸው ቡድኖች ጋር የተደረጉ ጨዋታዎች ነበሩ። ነገ ግን ተጋጣሚዎቹ ቢያንስ ግብ እስኪያስቆጥሩ የተሻለ ክፍት የሆነ እና በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ጨዋታ እንደሚያስመለክቱን ይጠበቃል። ሆኖም ሁለቱም በማጥቃቱ ረገድ ያላቸው ጥንካሬ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆኑ በፍልሚያቸው ውስጥ በርካታ የግብ ዕድሎችን እና ግቦችን የማየታችን ጉዳይ አጠራጣሪ ይመስላል። ያም ቢሆን በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ደርሰው የሚቸገሩባቸው ነጥቦች የተለያዩ ይመስላሉ።
አዳማ ከተማ ኳስ መስርቶ የመጫወት ዝንባሌ ቢታይበትም በማጥቃት ሂደት ውስጥ የመቻኮል ድክመት ይታይበታል። ቡድኑ ወደ ማጥቃት ሲሸጋገር ጥድፊያ ውስጥ ሲሆን ቢታይም ሂደቱን በስኬት አጠናቆ ወደ ግብ ዕድልነት ሲፈጥር የማይታይ በመሆኑ አጥቂዎቹ እንደልብ አጋጣሚዎች አግኝተዋል ለማለት አያስደፍርም። ሀዲያ ሆሳዕናም ተመሳሳይ ችግር ቢስተዋልበትም ከነገ ተጋጣሚው የተሻለ ወደ ግብ አፋፍ ሲደርስ ይታያል። ሆኖም ቡድኑ አሁን ላይ ከውጤት መራቁ ያመጣው ችግር በሚመስል መልኩ አጥቂዎቹ ዕድሎችን ሳይጠቀሙ ሲቀሩ ተመልክተናል።
ከእነዚህ ድክመቶች በመነሳት የነገውን ጨዋታ ስናስብ በዋነኝነት አዳማ ከተማ ሦስተኛው ሜዳ ላይ ያለውን ይቅብብል ስኬት ማሻሻል ሆሳዕናም የአጨራረስ ችግሩን አርሞ መቅረብ እንደሚኖርባቸው እንረዳለን። ከቡድኖቹ የጨዋታ ምርጫ አንፃር ግን ከመስመር ባለፈ መሀል ለመሀል የሙሰነዘሩ ጥቃቶች በተለይ በአዳማ ብኩል የመታየት ዕድል ይኖራቸዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ተጋጣሚ የመከላከል ቅርፁን ሳያገኝ ኳስ መስርቶ የመውጣት ፍጥነት የሚኖረው ቡድን ውጤት የማግኘት ዕድሉ የሰፋ ነው። ይህንን ነጥብ ስናስብ ቁልፍ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾቻቸውን ግልጋሎት የማያገኙት አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ሰውን በሰው ከመተካት ባለፈ የአቀራረብ ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ሊገቡ የሚችሉበትም ዕድል ይኖራል።
በተጨዋቾች የተናጠል ትኩረት ደግሞ አምና ከሆሳዕና ጋር የነበረው ዳዋ ሆቴሳ በብሔራዊ ቡድን ካደረገው የመጀመሪያ ተመራጭነት ተሳትፎ በኋላ ወደ አዳማ ሲመለስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተጠባቂ ነው። እንደ ዑመድ ዑኩሪ እና ባዬ ገዛኸኝ ያሉ የነብሮቹ አጥቂዎችም የቡድናቸውን የእስካሁኑ ጉዞ ለማስተካከል ወሳኝ የሆነውን የግብ መንገድ ከነገው ጨዋታ ሊያገኙ ይችላሉ።
አዳማ ከተማ ያለምንም የቅጣት እና ጉዳት ዜና ጨዋታውን ሲከውን በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ቅጣት ሄኖክ አርፌጮ ደግሞ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል ። ከዚህ በተጨማሪ የባዬ ገዛኸኝ መሰለፍ ያልለየለት ሲሆን ኤፍሬም ዘካሪያስም ከስብስቡ ጋር አይገኝም።
ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ ምስጋናው መላኩ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን አራት የሊግ ግንኙነት ታሪክ ሲኖራቸው አዳማ ከተማ ሁለቴ ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ አንዴ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታዎቹ አስር ግቦች ሲመዘገቡ ሀዲያ የአራቱ አዳማ የስድስቱ ባለቤት ሆነዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)
መሳይ አያኖ
ብርሃኑ በቀለ – ፍሬዘር ካሳ – ኤሊያስ አታሮ – እያሱ ታምሩ
ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ክብረአብ ያሬድ
ሀብታሙ ታደሠ – ባዬ ገዛኸኝ – ፀጋዬ ብርሃኑ
አዳማ ከተማ (4-3-3)
ሴኮባ ካማራ
ሚሊዮን ሰለሞን – አሚን ነስሩ – ቶማስ ስምረቱ – ደስታ ዮሐንስ
ኤሊያስ ማሞ – ዮሴፍ ዮሃንስ – አማኑኤል ጎበና
አሜ መሐመድ – ዳዋ ሆቴሳ – አብዲሳ ጀማል