ሪፖርት | የወረደ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ሀዲያ እና አዳማ ነጥብ ተጋርተዋል

በአራተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሁለተኛ መርሐ-ግብር የተገናኙት ሀዲያ እና አዳማ የወረደ ፉክክር አሳይተው ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

በሦስተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች የዓመቱ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት ከመጨረሻው ጨዋታ ሔኖክ አርፊጮ፣ ኤሊያስ አታሮ፣ ሀብታሙ ታደሠ እና ፍቅረእየሱስ ተወልደብርሃንን በቃለአብ ውብሸት፣ መላኩ ወልዴ፣ አበባየሁ ዮሐንስ እና ኢያሱ ታምሩ ለውጠዋል። በወላይታ ድቻ ተሸንፈው የመጡት አዳማ ከተማዎች ደግሞ በግብ ብረቶቹ መካከል የሚቆመውን ሴኩምባ ካማራን በጀማል ጣሰው ተከላካዩ አሚኑ ነስሩን በጀሚል ያቆብ እንዲሁም አጥቂው አቡበከር ወንድሙን በአብዲሳ ጀማል ተክተዋል።

ጨዋታው እንደተጀመረ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ወደ ሳጥን ያሻሙንት ኳስ የመጀመሪያ ጨዋታውን እያደረገ የነበረው ጀማል ጣሰው በአግባቡ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ገና በጊዜ ግብ ሊቆጠር ነበር። በአምስተኛው ደቂቃ ደግሞ ፍሬዘር ካሣ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ዳዋ ሁቴሳ ለመጠቀም ጥሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። በተለይ ሀዲያ ፈጣኖቹን አጥቂዎቹን በመጠቀም መሪ ለመሆን ቢታትርም ሀሳቡ ሳይሰምር ጨዋታው ቀጥሏል። በ15ኛው ደቂቃ ግን ዑመድ ከባዬ ገዛኸን ተቀብሎ በግራ እግሩ የመታው ኳስ ግብ ከመሆን የመከተው ጀማል ጣሰው ነበር።

እንደ አጀማመሩ ሙከራዎችን በማስተናገድ ያልቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መሐል ሜዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴ በማስመልከት እስከ 43ኛው ደቂቃ ድረስ ተጉዟል። በዚህ ደቂቃ ግን አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔ የታየበት ቅፅበት ተከስቷል። በዚህም የሀዲያ ተከላካይ ለግብ ጠባቂው አሳጥሮ የላከውን ኳስ ፈጣኑ አጥቂ ዳዋ ደርሶበት ለመጠቀም ሲጥር ኳሱን ለመከላከል የፍፁም ቅጣት ምት ክልሉን ለቆ የወጣው የግብ ዘቡ ሶሆሆ ሜንሳ ኳሱን በእጁ አቅጣጫውን ያስተዋል። አጋጣሚውን ተከትሎ የአዳማ ተጫዋቾች ለግብ ጠባቂው ቀይ ካርድ ይሰጠው ቢሉም የዕለቱ ዋና ዳኛ ምስጋናው መላኩ ጥፋቱን በመጀመሪያ የማስጠንቀቂያ ካርድ (ቢጫ) አልፈውታል።

ክለቡም ውሳኔው ልክ አይደለም በሚል ወዲያው ክስ አሲዟል። የሆነው ሆኖ የተገኘውን የቅጣት ምት ዳዋ ለመጠቀም ጥሮ ለጥቂት ዒላማውን ስቶበታክ። የመጀመሪያው አጋማሽም እጅግ አሰልቺ በሆነ መልኩ አንድ ብቻ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አስተናግዶ ተገባዷል።

ሳቢ እንቅስቃሴ ማስመልከት ያልቻለው ይህ ጨዋታ አሁንም ከሙከራዎች የራቀ ነበር። በ57ኛው ደቂቃ ግን አዳማ ከተማ በራሱ በኩል የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጓል። በዚህ ደቂቃም የመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ሌላ የቅጣት ምት አግኝቶ የነበረው ዳዋ አሁንም ከጥሩ ቦታ አግኝቶ መሬት ለመሬት ቢመታውም ሶሆሆ ወደ ውጪ አውጥቶበታል። በአንፃሩ ግን አዳማ ከተማ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ተሽሎ በመገኘት ጨዋታውን ማድረግ ይዟል።

በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ብልጫ የተወሰደባቸው ሀዲያዎች በ66ኛው ደቂቃ እንደ አዳማ ባገኙት የቅጣት ምት ቀለል ያለ ሙከራ አድርገው ነበር። በዚህም የአማካይ መስመር ተጫዋቹ አበባየሁ የመታውን ኳስ ጀማል ሳይቸገር አድኖታል። በ77ኛው ደቂቃ ደግሞ የግራ የአዳማ የፍፁም ቅጣት ምት ክፍል ላይ ዑመድ ያገኘውን ኳስ በግራ እግሩ አመቻችቶ በቀኝ እግሩ ወደ ግብ ቢልከውም መረብ ላይ ሳያርፍ ቀርቷል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ በ50ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ የማስጠንቀቂያ ካርድ (ቢጫ) አይቶ የነበረው ተከላካዩ መላኩ ወልዴ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አቡበከር ወንድሙ ላይ ሌላ ጥፋት ሰርቶ በሁለት ቢጫ ካርድ (ቀይ) ከሜዳ ተሰናብቷል። በቀሩት ደቂቃዎች አዳማ የማታ ማታ ያገኘውን የቁጥር ብልጫ ለመጠቀም ቢጥርም ሳይሳካለ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ጨዋታው ሲጀመር የነበራቸውን አንድ ነጥብ ከጨዋታው በኋላም ይዘው የወጡት ሀዲያ እና አዳማ በቅደም ተከተላቸው አስራ ሦስተኛ እና አስረኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።