የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 0-0 አዳማ ከተማ

ደካማ እንቅስቃሴ አስመልክቶን ያለጎል ከተጠናቀቀው የሀዲያ ሆሳዕና እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞቹ ለስፐር ስፖርት ተከታዩን አስተያየት አጋርተዋል።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምኅረት – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ

ከሞላ ጎደል አሁንም ትልቁ ችግራችን ጎል ማስቆጠር ነው። ዛሬም ያለጎል ጨዋታው ተጠናቋል። መጀመርያ ከጨዋታው በፊት እንደተናገርኩት ጠንከር ይላል። ያው አሁንም ፊት ላይ ደጋግመን እንሰራለን። ለቀጣይም ጨዋታ የተሻለ ነገር ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን። ዛሬ በብዙ መንገድ ደስ ብሎኛል ልጆቼ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል።

የአማካይ ቁጥር በማብዛቱ የሚፈለገውን ስለማግኘታቸው

ሲጀመር ጥሩ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ተመሳሳይ ነበር። አጋጣሚ ሆኖ የምትፈልገውን ለማግኘት ብዙ የሚመቹ ነገሮች ከሌሉ ትቸገራለህ። በእርግጠኝነት የምናገረው ተጫዋቾቼ ተሟልተው ሲመጡ የምፈልገውን ነገር አገኛለው ብዬ አስባለው።

እስካሁን ሦስት ነጥብ ባለማገኝታቸው ጫና ውስጥ ገብተው ይሆን

በፍፁም ምንም የሚያሳስብ ነገር የለም። እስካሁን በቡድኔ ደስተኛ ነኝ ነገ ማሸነፍ እንደሚችል ማሳየት የሚችል ቡድን ነው። በቀጣይ ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት እናገኛለን። ጠዋት እና ማታ ሰርተን የሚጎሉንን አስተካክለን እንመጣለን እንጂ በፍፁም የሚያሳስበኝ ነገር አይኖርም።

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ

ስለጨዋታ እንቅስቃሴ

መጥፎ ጨዋታ አልነበረም። የመጀመርያው አጋማሽ ጨዋታው እንዳሰብኩት አልነበረም። በሁለተኛው አጋማሽ የታክቲክ ለውጥ አድርገን ጎል ለማግኘት ሞክረናል። ከመሸነፍ ነበር የመጣነው ሙሉ ሥስት ነጥብ ለማግኘት አስበን ነበር። ሆኖም አልተሳካልንም።

ከመስመር ውጭ ግብጠባቂው ሜንሳህ ኳስ አስቀርቶ በቢጫ መታለፉ ቡድኑ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ

ግልፅ ነው፤ በዚህ ላይ መነጋገር አያስፈልግም። ህጉን መተርጎም ነው። ባለፈው ጨዋታ በዳኝነት ስህተት ተሸንፈን ወጥተናል። ዛሬ ደግሞ ግልፅ የዳኝነት ስህተት ታይቷል። በተፈጥሮዬ በዳኝነት የማሳብብ አሰልጣኝ አይደለሁም። ግን እየደከምክ እየመጣህ በዳኝነት ስህተተ ውጤት የምታጣ ከሆነ የሊጉን ደረጃ ይቀንሰዋል። ሁሉም ሰው እኩል መዳኘት አለበት ብዬ አስባለው። የዛሬው በእኔ ስህተት ነው ብዬ አላስብም፤ ህግ መተርጎም ብቻ ነበር የሚያስፈልገው። በዳኝነቱ አዝኛለው።

ቡድኑ እስካሁን ባደረገው ጨዋታ የወሰደው ተሞክሮ

እንደምታዩት ቡድናችን አዲስ ነው። ከአራቱ ጨዋታዎች የምንፈልገውን ውጤት አግኝተናል ብዬ አላስብም። ግን ቢሆንም ጨዋታዎች ሲያልፉ መማርያዎች ይሆናሉ። ሜዳ ውስጥ እጅ ላለመስጠት የሚታገል ቡድን ስለነበረ ያንን በውጤት ለማገዝ ባሉን ጊዜያት እንሰራለን።