ፌዴሬሽኑ ከጀርመን ተቋም ጋር በታዳጊ ስልጠና ዙርያ አብሮ ለመሥራት ይፋዊ ስምምነት አደረገ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለአምስት ዓመት የሚቆይ ብሔራዊ የታዳጊዎች ስልጠና ፕሮጀክትን ከ3POINTS ተቋም ጋር ለመሥራት ስምምነት አድርጓል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በታዳጊዎች ልማት ላይ ትኩረቱን በማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመዘርጋት በትግበራ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በዛሬው ዕለት በጂፒተር ሆቴል ትልቅ ዓላማ እንዳነገበ የተነገረለት ስምምነትን ከጀርመኑ 3POINTS ተቋም ጋር አድርጓል።

በይፋዊ ስምምነቱ ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ፣ የፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ሲገኙ በ3POINTS በኩል ዋና ኃላፊው ታደሰ ሳሙኤል እንዲሁም ወላጅ አባት እና እናቱ ተገኝተዋል።

በዚህ ስምምነት ላይ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ገፅታ ላይ ዝርዝር ገለፃ የተደረገ ሲሆን ዋና ዋና ነጥቦቹ የሚከተሉት ናቸው፦

3POINTS ጀርመን ሀገር መሰረቱን ያደረገ የእግርኳስ ተጫዋቾች ወኪል ነው። ዋናው የፕሮጀክቱ ዓላማ ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች መቶ የሚጠጉ ታዳጊዎችን በማሰልጠን ለብሔራዊ ቡድኖቻችን፣ አልፎም ለታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች ገበያ ማብቃት ትኩረቱን ያደረገ ነው። የፕሮጀክቱ የሚካሄድበት ስፍራ የካፍ የልህቀት ማዕከል ጊቢ ውስጥ ባለ ክፍት መሬት ላይ ሲሆን ለግንባታው ወደ ስድስት ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግበት ተገምቷል። ፌዴሬሽኑ እና 3POINTS 50/50 ወጪ የሚሸፍኑም ይሆናል። የፕሮጀክቱ ስምምነት ለአምስት ዓመት ሲቆይ እድገቱ እየተገመገመ እንዲቀጥል ይደረጋል።

ለፕሮጀክቱ አሰልጣኞች ተመርጠው ለሚመጡት 100 ሰልጣኞ የትምህርት፣ የቀለብ እና የህክምና ወጪ ሙሉ ለሙሉ የሚሸፍነው 3POINTS ካምፓኒ ይሆናል። በሚወጣው መስፈርት መሰረት የተመረጡት ሰልጣኞች በስልጠናው ሂደት በሚያሳዩት ወቅታዊ አቋም እድገት የሚያሳዩ ከሆነ በፕሮጀክቱ የሚቀጥሉ ሲሆን ሆኖም ግን መሻሻል ያላሳዩትን በመቀነስ በየጊዜው ምልመላ የሚካሄድ መሆኑ ሲገለፅ ባቱ ላይ በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ በተቋቋመው ቴክኒክ ኮሚቴ የተመረጡ ሀምሳ ታዳጊዎች ወደዚህ ፕሮጀክት የሚቀላቀሉ ይሆናል።

በተቀመጠው የዝውውር ፖሊሲ መሠረት ታዳጊዎቹ ዕድል ቀንቷቸው ወደ አውሮፓ ክለቦች የሚያቀኑ ከሆነ ከዝውውሩ ከሚገኘው ገቢ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አርባ በመቶ፣ 3POINTS ደግሞ ስልሳ በመቶ የሚወስዱ እንደሆነ ከመድረኩ ተገልፇል።

አቶ ኢሳይያስ ጅራ ስምምነቱን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት “የፌዴሬሽኑ የረጅም ጊዜ ህልም እውን ሆኗል። እነርሱ እንደሚሉት ባህሩ ውስጥ አሳው አለ። አሳውን ማጥመዱን እኛ እንሰራለን በማለት ይህን ኃላፊነት በመውሰድ ነው ከእኛ ጋር ለመሥራት የመጡት። ይህ ፕሮጀክት በሥራ አስፈፃሚ ባለሙያዎች በደንብ ታይቶ ሀገር በሚጠቅም ሁኔታ ተቀርፆ የተዘጋጀ ነው። ትልቅ ፕሮጀክት፣ ትልቅ ግብ ነው ይዘን የተነሳነው። ምን አልባት ከተወሰኑ ዓመታት በኃላ ከዚህ ፕሮጀክት ወጥተው በአውሮፓ የሚጫወቱ አንድ ሁለት ኢትዮጵያውያን ልንመለከት እንችላለን። በቅርቡ ሥራው መሬት ወርዶ ፍሬውን ለማየት ትኩረት አድርገን እንሰራለን”። ብለዋል።

በማስከተል 3POINTS ባለቤት እና የፕሮጀክቱ ጠንሳሽ አቶ ታደሰ ስለ ፕሮጀክቱ እና በቀረበላቸው ጥያቄ ዙርያ ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተዋል፦

“የተወለድኩት ቢሾፍቱ ነው፤ ገና በሦስት ወር እድሜዬ ነበር ከቤተሰቦቼ ጋር ወደ ጀርመን ያቀናነው፤ ስሪ ፖይንትስ የተሰኘውን ድርጅት የተቀላቀልኩት የዛሬ 8 ዓመት ነበር። ድርጅቱም የሚሰራው በአውሮፓ የሚገኙ ጥራታቸው የላቁ ባለተሰጥኦ ተጫዋቾች ከክለቦች ጋር በመሆን ማብቃት ነው። በዚህ ሂደት ተጫዋቾቹ ከማሰልጠኛ አካዳሚዎች የመጀመርያው ፕሮፌሽናል ኮንትራታቸውን እስከሚፈራረሙ ድረስ እገዛ እናደርግላቸዋለን። እንደ ተምሳሌት የማየው ከአራቱ ልጆቼ የመጀመሪያው ወንዱ ልጄ ዳቪ ሰልከን ነው። እሱ አሁን 26 ዓመቱ ሲሆን በቡንደስሊጋው ለሀርታ በርሊን እየተጫወተ ይገኛል። ከአንደ ወዳጄ ጋር በመሆን ወኪሉም ማናጀሩም ሆነን እየሰራን እንገኛለን። እነ ዳቪ የመጡበትን መንገድ እዚህ ለመድገም እናስባለን፤ በአውሮፓ ክለቦች ታዳጊዎችን ከ13 (14) ዓመታቸው ጀምሮ በራሳቸው አካዳሚዎች በተሟላ ሁኔታ ሌት ተቀን ይሰራባቸዋል። ይህን አሰራር እዚህ ማምጣት ይኖርብናል።

“ቀዳሚው እቅዳችን ስሪ ፖይንትስ የተሰኘ አካዳሚ መገንባት ነው፤ ከመላ ሀገሪቱ የተሻለ አቅም ያላቸውን ተጫዋቾች መልምለን ወደ አዲስአበባ ወደሚገኘው አካዳሚያችን እናመጣቸዋለን። ከዚያም ልጆቹን ከአውሮፖ ከሚገኙ አጋሮቻችን ጋር በመሆን በተለያዩ እግርኳሳዊ መመዘኛዎች አቅማቸውን ለማሳደግ ሌት ተቀን እንሰራባቸዋለን። የመጨረሻው ግባችን የሚሆነው የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊ ተጫዋች በአውሮፓ ወደ ሚገኝ ትልቅ ሊግ ማዘዋወር መቻል ነው ይህንን ታሪክ ለመስራት ቆርጠን ተነስተናል።

“እንደ መነሻ ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች ታዳጊዎች ለመጀመር ነው ያቀድነው፤ የምናዘጋጀው አካዳሚ ለ100 ታዳጊዎች የሚሆን ነው። ስንጀምር ግን በ50 ታዳጊዎች ነው። በቀጣይ ከአንድ ዓመት ተኩል በኃላ ከዚህ ባነሱ ዕድሜዎች ስልጠናውን የማስፋት እቅድ አለን።” ብለዋል።

በመጨረሻም የሚገነባውን የአካዳሚውን ህንፃ ንድፈ ሀሳብ በምስል ለታዳሚዎቹ ከታየ በኃላ በሁለቱ አካላት የስምምነት ፊርማ ስነ ስርዓቱ ተከናውኗል።

ያጋሩ