ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታን በሚከተለው ምልኩ ዳሰነዋል።

በሦስቱ የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ድል ያስመዘገቡት ወላይታ ድቻዎች በተከታታይ ያገኙት የድል ቁጥር ወደ ሦስት በማሳደግ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት አካባቢ ለመዝለቅ ነገም ጠንክረው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታሰባል።

ቀጥተኛ አጨዋወትን አዘውትረው ሲከተሉ የሚታዩት ወላይታ ድቻዎች ነገም በዚሁ የአጨዋወት ባህሪያቸው ጨዋታውን እንደሚቀርቡ ይገመታል። በተለይ ተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡና ከኳስ ጋር ዘለግ ያለውን ጊዜ ማሳለፍ የሚሻ ቡድን ስለሆነ ኳሱን ለቀው በወሳኝ የጨዋታ ቅፅበቶች ላይ ብቻ ከኳስ ጋር ሊያሳልፉ ይችላሉ። ይህ ቢሆንም ግን ለበርካታ ጨዋታዎች ቡናዎች ሲቸገሩበት የሚታየውን የኳስ ምስረታ ድቻዎች ትልቅ ትኩረት ሰጥተውበት እንደሚገቡ እሙን ነው። በዋናነት ደግሞ ከወገብ በላይ ያሉት የቡድኑ ፈጣን ተጫዋቾች የቡና ተከላካዮችን እና አማካዮችን የኳስ ቅብብል መንገድ በአግባቡ የሚዘጉ ከሆነ እምብዛም ሌሎች አማራጮችን ሲከተል የማይታየውን ቡድን ለስህተት ሊዳርጉ ይችላሉ።

ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን አሸንፈው በጥሩ የማሸነፍ ሥነ-ልቦና ላይ ተገኝተው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ሊጉ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች መቋረጡ መንገዳቸውን እንዳያጠፋባቸው ያሰጋል። እርግጥ ይህ ሁሌ ባይከሰትም አልፎ አልፎ የጨዋታዎች መቆራረጥ ለቡድኖች እንደያሉበት ሁኔታ አሉታዊ እና አዎንታዊ ጥቅም ሊሰጥ ይችላል። የሆነው ሆኖ ቡድኑ ስንታየሁ መንግስቱን ዒላማ ያደረጉ ኳሶች በመላክ ነጥብ ይዞ ለመውጣት እንደሚታትር ሲገመት ከኳስ ውጪ ግን ችምችም ብሎ በራሱ ሜዳ እንደሚቆይ ይታሰባል።

በቡድኑ ውስጥ ምንም ቅጣት የሌለ ሲሆን ተከላካዩ አንተነህ ጉግሳ በቤተሰብ ሀዘን ምክንያት እንዲሁም ሁለተኛ እና ሦስተኛ የግብ ዘብ የሆኑት ቢኒያም ገነቱ እና ወንድወሰን አሸናፊ ጉዳት ላይ በመሆናቸው ከነገው ፍልሚያ ውጪ ናቸው።

እስካሁን ከድል ጋር ካልተገናኙት አራት የሊጉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና የዓመቱን የመጀመሪያ ድል በማስመዝገብ አምና ወደ ነበረበት ጠንካራ ብቃቱ ለመመለስ ጠንክሮ ጨዋታውን እንደሚቀርብ ይገመታል።

በአሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና ከዓምና ብቃቱ በተለየ ሁኔታ ፍጥነት አልባ አጨዋወት ሲጫወት በሦስቱ ጨዋታዎች ታይቷል። በተለይ ቡድኑ ኳስ ሲመሰርት ከነበረው ዝግታ በማይተናነስ ሁኔታ በተጋጣሚ ሜዳ ሲገባም የሚስተዋልበት እርጋታ መጠኑን ያለፈ መሆኑ ተጋጣሚን የመደራጃ እና ክፍተት የመዝጊያ ጊዜ እየሰጠው ይገኛል። ይህንን ችግር ምናልባት ቡድኑ በነበሩት የ20 ቀናት የእረፍት ጊዜ ቀርፎ ከመጣ ግን አደገኝነቱ አይቀሬ ነው። ከምንም በላይ ቦታዎችን ቶሎ ቶሎ እየተቀያየሩ የሚጫወቱት የቡድኑ ከወገብ በላይ የሚገኙ ተጫዋቾች የድቻን ተከላካዮች ትኩረት በማሳቱ ረገድ የሚኖራቸው ብቃት ምናልባት ነገ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ሊሆን ይችላል።

በሦስቱ የሊጉ ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ ያስቆጠረው ኢትዮጵያ ቡና የአጥቂ መስመሩ ላይ እየተነሱ ያሉትን ጥያቄዎች በነበረው የእረፍት ጊዜ ፈቶ እንደሚመጣ ይታሰባል። በተለይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአንድ የውድድር ዘመን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋችን (አቡበከር ናስር) በስብስቡ ይዞ ጎል ፊት አይናፋር መሆኑ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል። ይህ ጉልህ ክፍተት ደግሞ ቶሎ መሻሪያ ካላገኘ ቡድኑ ነገም ሊቸገር ይችላል።

ቡናማዎቹ በነገው ጨዋታ የሬደዋን ናስር፣ አላዛር ሺመልስ፣ ሚኪያስ መኮንን እና ነስረዲን ኃይሉን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት እንደማያገኙ ታውቋል።

ይህንን ጨዋታ ፌዴራል ዋና ዳኛ አዳነ ወርቁ በአልቢትርነት እንደሚመሩት የወጣም ፕሮግራም ያሳያል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ በሊጉ ለ14 ጊዜያት ተገናኝተዋል። በግንኙነታቸውም የተሻለ ሪከርድ ያለው ወላይታ ድቻ ነው። በዚህም ድቻ አራት ጊዜ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ሦስት ጊዜ ድል አግኝቷል። በቀሪዎቹ ሰባት ግንኙነቶች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸው ኢትዮጵያ ቡና 11 ወላይታ ድቻ ደግሞ 10 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (3-5-2)

ፅዮን መርዕድ

በረከት ወልደዮሐንስ – ደጉ ደበበ – በረከት ቦጋለ

ያሬድ ዳዊት – እድሪስ ሰዒድ – ንጋቱ ገብረሥላሴ – ሐብታሙ ንጉሤ – አናጋው ባደግ

ምንይሉ ወንድሙ – ስንታየሁ መንግሥቱ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – ቴዎድሮስ በቀለ – አበበ ጥላሁን – አስራት ቱንጆ

ሮቤል ተክለሚካኤል – አማኑኤል ዮሐንስ – ታፈሰ ሰለሞን

አቤል እንዳለ – እንዳለ ደባልቄ – አቡበከር ናስር