የነገውን ሁለተኛ ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንዲህ አሰናድተንላችኋል።
በሳምንቱ ሦስተኛ የጨዋታ ዕለት ከዕረፍት ወደ ሜዳ የመመለስ ተራው የምዕራብ እና ምስራቅ ቡድኖቹ ጅማ እና ድሬዳዋ ይሆናል። የመጨረሻ ግጥሚያቸው ላይ የተቃረነ እንቅስቃሴ ያደረጉት ጅማ አባ ጅፋር እና ድሬዳዋ ከተማ እርስ በእርስ ሲገናኙ ውጤት የማግኘት ጫናው ወደ ጅማ ያዘነብላል። እስካሁን ምንም ነጥብ ያላሳኩት ጅማዎች ከውጤት ማጣቱ ባለፈ በፋሲል ሰፊ ሽንፈት እንደደረሰባቸው ይታወሳል። በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ነጥብ ከመጋራትም በላይ ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ማድረጋቸው አይዘነጋም።
የቡድኖቹን የእስካሁኑ አመጣጥ ስንመለከት ጅማ አባ ጅፋር ነገ የመልሶ ማጥቃት አዝማሚያ እንደሚኖረው ይገመታል። የኳስ ቁጥጥር ፍላጎት ያለው ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በዚሁ አኳኋን ወደ ፊት ገፍቶ ለመጫወት እንደሚጥር ይታሰባል። በዚህ ሂደት ጅማዎች በመከላከል ሽግግር ወቅት ጨዋታውን በጀመሩበት የትኩረት ደረጃ መቀጠል አለመቻላቸው ከፋሲል ከነማ ጋር ዋጋ ሲያስከፍላቸው ታይቷል። ይህ በመሆኑ ደግሞ ከመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ መነሻቸውን አድርገው በሁለቱ መስመሮች የሚመጡ ጥቃቶችን መቋቋም ሲያቅታቸው አይተናል። ይህ ድክመት ተሻሽሎ ካልመጣ በማጥቃት ወቅት የመስመር ተሰላፊዎቹን አብዝቶ ሲጠቀም ያስተዋልነው ድሬዳዋ የግብ ዕድሎችን እንዲያገኝ በር መክፈቱ የሚቀር አይመስልም።
ድሬዳዋ የውጪ ዜጎቹን የወረቀት ሥራ አጠናቆ መጠቀም መጀመሩ ጥሩ ጥንካሬ ፈጥሮለት ታይቷል። ይህ ነጥብ በጨዋታው አጠቃላይ መንገድም ሆነ በተስላፊዎች ምርጫ ላይ በወጥነት እንዲቀጥል የሚረዳው በመሆኑ በነገው ጨዋታ የተሻለ የውህደት ደረጃ እንደሚያስመለክተን ይጠበቃል። ወደ ጅማ ስንመለከት ግን ሰፊ ክፍተት እናገኛለን። በአዳዲስ ተጫዋቾች የተገነባውን ቡድን በዚህ አጭር ጊዜ መልክ ማስያዝ ለአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቀላል የሆነ አይመስልም። ከፋሲል ጋር ከሦስት የተከላካይ መስመር ወደ አራት በመምጣት የቅርፅ ለውጥ አድርገውም ውጤቱ እንደሚፈለገው አልሆነም። ነገም ሌላ አማራጭ በመሞከር ቡድናቸው በቶሎ ወደ መስመር እንዲገባ ለማድረግ የተለየ መላ ይዘው የሚቀርቡበት መንገድ የሰፋ ነው።
ድሬዳዋ ከተማ ከዕረፍት ጊዜው በኋላ በጊዮርጊሱ ጨዋታ ምልክት የሰጠውን የኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ የማጥቃት ሂደቱን በግብ ዕድሎች ለማጀብ የሚረዳውን መሻሻል አድርጎ እንደሚመለስ ይጠበቃል። በጅማ በኩልም ከበርካታ ክፍተቶቹ ዋናው የሆነውን ከኳስ ውጪ ሲሆን የሚታይበትን ያለመረጋጋት ማስወገድ በማጥቃቱም ፊት ላይ ያለውን የወጣት እና አንጋፋ ጥምረት ወደ ውጤታማነት ማምጣት በቶሎ ካለበት ደረጃ ለማገገም ቁልፍ የትኩረት ሀሳቦቹ ይመስላሉ።
ጅማ አባ ጅፋር ዳዊት እስጢፋኖስን በቅጣት ከማጣቱ ባሻገር ጉዳት ላይ ቆይተው ቀላል ልምምድ የጀመሩት ሽመልስ ተገኝ እና ኢዮብ ዓለማየሁን ግልጋሎትም አያገኝም። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ ዳንኤል ኃይሉ እና ሔኖክ አየለ ጉዳት ላይ ሲሆኑ የማማዱ ሲዲቤ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።
ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ በፀጋው ሽብሩ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ድሬዳዋ እና ጅማ ከስድስት ግንኙነታቸው በአንዱ ብቻ አቻ በተለያዩበት ታሪካቸው ድሬዳዋ አራት ጊዜ ጅማ ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታዎቹ ድሬዎች ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥሩ ጅማዎች ደግሞ አራት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ጅማ አባጅፋር (4-2-3-1)
ዮሐንስ በዛብህ
ዱላ ሙላቱ – በላይ አባይነህ – ያብስራ ሙሉጌታ – አስናቀ ሞገስ
ሮጀር ማላ – ተስፋዬ መላኩ
ሱራፌል ዐወል – መስዑድ መሀመድ – መሀመድ ኑርናስር
ዳዊት ፍቃዱ
ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)
ፍሬው ጌታሁን
እንየው ካሳሁን – መሳይ ጳውሎስ – አውዱ ናፊዩ – ሄኖክ ኢሳይያስ
ብሩክ ቃልቦሬ – ዳንኤል ደምሴ
ጋዲሳ መብራቴ – ሙኸዲን ሙሳ – አብዱለጢፍ መሀመድ
ማማዱ ሲዲቤ