የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለው ጅማ አባጅፋር አራት ተጫዋቾችን በውሰት ውል ወደ ክለቡ ሲቀላቅል የሀላባ ከተማውን ወጣት አማካይ በቢጫ ቴሴራ አስፈርሟል፡፡
በ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ እየተካፈለ የሚገኘው እና ባደረጋቸው ሶስት የሊጉ መርሃግብር አንድም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻለው የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለው ጅማ አባጅፋር የመጀመሪያውን ድል ለማሳካት ዛሬ ምሽት 1፡00 ድሬዳዋ ከተማን በአራተኛው ሳምንት ጨወታ ይገጥማል፡፡ ያለፉትን ሳምንታት ለበርካታ ተጫዋቾች ሙከራ ሲሰጥ የነበረው እና በሙከራው አመርቂ አቅምን ማሳየት ከቻሉ ተጫዋቾች መሀል የኢትዮጵያ ቡናውን ሙሴ ካባላን ማስፈረሙን ከደቂቃዎች በፊት ገልፀን የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ አራት ወጣት ተጫዋቾችን እስከ ዓመቱ መጨረሻ በውሰት ውል ወደ ቡድኑ ሲቀላቅል አንድ ተጫዋችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል፡፡
2010 በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና በሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴካፋ ዋንጫ በዩጋንዳው ውድድር የብሔራዊ ቡድኑ አባል የነበረው እና የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ ያጠናቀቀው የሀዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ እና ዘንድሮ ከ20 ዓመት በታች የሀዋሳ ቡድን ወደ ዋናው አድጎ የነበረው አማካዩ ብሩክ ዓለማየሁ፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን የተገኘው የመስመር ተከላካዩ ምስጋናው መላኩ እና በተመሳሳይ ከፈረሰኞቹ ታዳጊ ቡድን የተገኘው ትንሳኤ ይርጌሳ በውሰት ውል ጅማ አባጅፋርን መቀላቀል የቻሉ ሲሆን አብዱልሰመድ መሐመድ የተባለ ተጫዋች ደግሞ ከከፍተኛ ሊጉ ክለብ ሀላባ ከተማ በአንድ ዓመት የቢጫ ቴሴራ ውል የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለው ቡድን አስፈርሟል፡፡