ወላይታ ድቻ ኢትዮጵያ ቡናን ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።
ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ
የሚፈልገውን ነገር ስለማግኘቱ
“አሁን ላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ለውጤት ነው። ኢትዮጵያ ቡና በተሻለ መነሳሳት ተለውጦ እንደሚመጣ አውቅ ነበር። ሁሉን ነገር ለማድረግ የሚያስችሉ ነገሮች በእጃቸው አለ። ያንን እንዳይጠቀሙ ከልክለናቸዋል። በዋነኝነት በረኛቸውን እንዳይጠቀሙና ትርፍ ሰው እንዳያገኙ አድርገናቸዋል ፣ ኳስ ስናጣ ቶሎ ብለን ሳጥናችንን እንዳያገኙ የምንዘጋቸው ቦታዎች ነበሩ። ዞሮ ዞሮ ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ ሆነን ተጫውተናል። በውጤቱም ደስተኛ ነኝ። በሽንፈት ጀምረን የዛሬው ድላችን ሦስተኛ ተከታታይ ድል ነው። ይህም የክለቡን ስነልቦና ለመመለስ ይጠቅመናል።”
በነጥብ ከመሪው ስለመስተካከላቸው
“እኛ እያንዳንዱን ጨዋታ የጥሎ ማለፍ ባህሪ ሰጥተን ነው የምንጫወተው ይህ የት እንደሚያደርሰን ባናውቅ በየጨዋታው ስህተቶቻችን እየቀረፍን ለመጫወት እንሞክራለን።”
ስለ ስንታየሁ መንግሥቱ
“በተጫዋችነት ዘመኔ አጥቂ ስለነበርኩ ለአጥቂ የራስ መተማመን መስጠት ነው የምፈልገው። ከገባቸው ኳሶች ይልቅ በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኛቸው የተሻሉ ናቸው። በእረፍትም ይህን ነገርዋለሁ አሁንም ቢሆን ከእነ ሙሉ ጤንነቱ አይገኝም። እንደዛም ቢሆን የጎል ሰው መሆኑን አሳይቷል።”
ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና
ስለጨዋታው
“ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ ከውጤቱ በስተቀር ሜዳ ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር።”
በመከላከሉ ስለነበረባቸው ክፍተቶች
“በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት እድሎችን አግኝተው ነበር ፤ ስንጫወት የምንከፍታቸው ቦታዎች አሉ እነሱን ለመጠቀም ይሞክሩ ነበር በተጨማሪም በተወሰኑ የሰራናቸው የአቋቋም ስህተቶች ነበሩ። ዋናው ነገር ወደ ፊት የሚሄዱ ኳሶች እንዳይባክኑ ማድረጉ ነው የሚባክኑ ኳሶች ካሉ ተጋጣሚ የተከፈቱ ሜዳዎችን ሊጠቀምበት የሚችልበት እድል ይኖራል እነዚህም የሚስተካከሉ ናቸው ብዬ አስባለሁ።”
ወላይታ ድቻን ለማስከፈት ስለመቸገራቸው
“አዎ ብዙ ለመጠቀም የፈለግነው መስመሩን ነበር ያው ሜዳውም አስቸጋሪ ነው ነገርግን ቡድኖች እንዲህ ተከማችተው ሲከላከሉ መስመሩን ይለቃሉ ያንንም ለመጠቀም ነበረውን ያሰብነው አልተሳካም።”
ጫና ውስጥ ስለመሆኑ
“ምናልባት ልጆቹ ላይ ቡና ለውጤት የሚጠበቅ ከመሆኑ ጋር ጫና ሊኖር ይችላል በተቻለን መጠን የምንፈልገውን ነገር ጠብቀው እንዲሄዱ የልጆቹን አምሮ መጠበቅን ይኖርብናል።”
ሁለተኛ ሙሉ የውድድር ዘመን እንደመሆኑ የቡድኑ የጨዋታ መንገድ በሚፈልገው መንገድ ስለማደጉ
“ሁሌም ቢሆን ተጋጣሚ የሚመጣበትን መንገድ ለማየት እንሞክራለን ግን ብዙም የተለየ ነገር የለም ተመሳሳይነት አላቸው አንዳንዴ የምንሰራቸው ስህተቶች ከሜዳው አመቺነት ጋርም ይያያዛሉ ፤ ያዝ ይህን እንደምክንያት ለማቅረብ ባይሆንም የተሻለ ሜዳ ቢኖር የእኛ ልጆች የሚሰሩትን ስህተት መቀነስ እንችላለን ይህም ተጋጣሚዎች የሚያገኙትን እድል መቀነስ እንችላለን። ቢሆንም ግን ጥሩ ነው ያለው ነገር።”