ሪፖርት | የማማዱ ሲዲቤ ሐት ትሪክ ድሬዳዋ ከተማን ባለ ድል አድርጓል

አራተኛ ተከታታይ ሽንፈት ላለማስተናገድ ጅማ አባጅፋሮች ከመጨረሻው የፋሲል ጨዋታ አራት ለውጦችን ሲያደርጉ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ፍልሚያ አንድም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል። እንደተጠቀሰው ጅማዎች ግን በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ሊጉ ሲቋረጥ በቢጫ ቴሴራ ያስፈረሟቸውን አላዛር ማርቆስ፣ ሙሴ ከበላ፣ ብሩክ አለማየሁ እና ትንሳኤ ያብጌታን በዮሐንስ በዛብህ፣ ተስፋዬ መላኩ፣ አስናቀ ሞገስ እና ሽመልስ ተገኝ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞ የድሬዳዋ ፖሊስ፣ ድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ፣ ድሬዳዋ ሴሜንት እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ለነበሩት (በ70’ዎቹ) ሻውል ኃይሌ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና በጊዜ መሪ አግኝቷል። በዚህም በአምስተኛው ደቂቃ የቀኝ መስመር ተከላካዩ እንየው ካሳሁን ከቀኝ የሳጥኑ ጫፍ ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ ለጅማ የመጀመሪያ ጨዋታውን እያደረገ የነበረው የግብ ዘቡ አላዛር ሺመልስ በሚገባ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ በሩቁ የግቡ ቋሚ የነበረው ማማዱ ሲዲቤ አግኝቶት ወደ ግብነት ቀይሮታል።

በድሬዳዋ ከተማ የውጤትም የእንቅስቃሴም ብልጫ የተወሰደባቸው ጅማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ በሚያደርጉት ጥረት ሁለተኛ ግብ አስተናግደው ፈተናቸው ብሷል። በዚህም በ23ኛው ደቂቃ ወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት ሔኖክ ኢሳይያስ ሲያሻማው ቁመታሙ አጥቂ ማማዱ ሲዲቤ ፈትልኮ በመውጣት የነካው ኳስ ከመረብ ጋር ተዋህዷል። አጀማመራቸው ያላማረላቸው ጅማዎች ግን በ34ኛው ደቂቃ እንየው ካሳሁን ዱላ ሙላቱ ላይ ጥፋት ሰርቶ በተገኘው እና በላይ አባይነህ በመታው የቅጣት ምት የመጀመሪያ ሙከራቸውን አድርገዋል። ነገርግን በላይ የመታው ኳስ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል።

ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን ይባስ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡበትን ሦስተኛ ግብ አስተናግደዋል። በዚህም በቀኝ በኩል በሚገኘው መዓዘን አካባቢ የተሰጠውን የቅጣት ምት መሐመድ አብዱለጢፍ ሲመታው ሳጥን ውስጥ ያሻውን እየፈፀመ የነበረው ማማዱ ሲዲቤ አግኝቶት ለራሱ እና ለቡድኑ ሦስተኛ ግብ አድርጎታል። ጅማ አባጅፋር ገና አጋማሹ ሳይጠናቀቅ ሦስት ግቦች እንዲቆጠሩበት ያደረገውን ክፍተት ለማሻሻል ሁለት ለውጦችን ቢያደርግም የተሻለ መንቀሳቀስ ሳይችል የመጀመሪያውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አገባዷል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች ያልነበሩበት ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቀዝቀዝ ባለ ግለት መካሄድ ጀምሯል። በአንፃሩ ጅማ አባጅፋሮች ግን ሻል ብለው ለመንቀሳቀስ በመሞከር ለመገልበጥ ከባድ የሆነውን ውጤት ለመቀየር ሲጥሩ ነበር። በተለይ በ57ኛው ደቂቃ መሐመድኑር ናስር ከዳዊት ፍቃዱ የተነሳውን ኳስ ከተከላካዮች አምልጦ ለመጠቀም የጣረበት እና ግብ ጠባቂው ፍሬው ቀድሞ ወቶ ያዳነበት አጋጣሚ ለግብ የቀረበ ነበር።

በቶሎ የሚፈልጉትን በእጃቸው ያስገቡት ድሬዳዋዎችም ጥቃቶችን መሰንዘር ጋብ አድርገው ከተንቀሳቀሱ በኋላ በ71ኛው ደቂቃ በአስፈሪ ሁኔታ ወደ ጅማ የመከላከል ወረዳ ተገኝተው ነበር። ከግራ የሳጥኑ ክፍል የተሻገረውን ኳስ ጋዲሳ መብራቴን ቀይሮ የገባው አብዱራህማን ሙባረክ ለመጠቀም ሲጥር የጅማ ተከላካዮች ሲያወጡት እንየው አግኝቶት ከርቀት ወደ ግብ ልኮት ነበር። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ተቀይሮ የገባው ኢዳላሚን ናስር የጅማን የማስተዛዘኛ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ሦስት ነጥብ የሸመቱት ድሬዎች ነጥባቸውን 7 አድርሰው ከ12ኛ ወደ 5ኛ ደረጃ ተስፈንጥረዋል። ጅማ አባጅፋሮች ደግሞ ያለ ምንም ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል።