የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታን የተመለከቱ ነጥቦችን እንዲህ አሰናድተናል።
የ2014 ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ታሪካዊዎቹን ክለቦች በማገናኘት ይቋጫል። በእንቅስቃሴ ብርቱ ፉክክር ሲደረግበት በሚስተዋለው የመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ የነገው ግንኙነት ጦሩ ወደ ሊጉ ከተመለሰ ወዲህ የመጀመሪያው ይሆናል። በውድድሩ እስካሁን ባለው ደረጃ ተጋጣሚዎቹ በሰንጠረዡ አጋማሽ አካባቢ ይገኛሉ። በተከታታይ ድል ሊጉን የጀመረው ጦሩ ከዕረፍቱ በፊት ሽንፈት ሲያስተናግድ ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ እስካሁን ድል ባይነሳም ሁለት የአቻ ውጤቶችን አስመዝግቧል። የጨዋታው ውጤት የነጥብ ስብስባቸውን ከፍ አድርጎ ቡድኖቹን ዳጎስ ያለ ደረጃ በማሻገር ወደ አናት የመግፋት ዕድሉ የሰፋ መሆኑ ሲታይ ፉክክሩ ከፍ ያለ ጨዋታ እንደሚሆን ተስፋ ይደረጋል።
ቡድኖቹ ያደረጓቾቸው የመጨረሻ ጨዋታዎች በአሰልጣኞቻቸው ተመሳሳይ አሉታዊ አስተያየቶችን ያስተናገዱ ነበሩ። ድንቅ አጀማመር አድርጎ ብዙ የተጠበቀው መከላከያ በአዲስ አበባ በሰፊ ጎል ሲረታ አሰልጣኝ ዮሀንስ ሣህሌ ስብስባቸው ለተጋጣሚ ዝቅ ያለ ግምት መስጠቱ ዋጋ እንዳስከፈላቸው በቁጭት ገልፀው ነበር። እንደዚሁ ሁሉ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቡድናቸው የወረደ የጨዋታ ፍላጎትን ማሳየቱ በድሬዳዋ ነጥብ እንዲጥሉ እንዳስገደዳቸው አንስተው ነበር። በመሆኑም ቡድኖቹ ተመሳሳይ መዘናጋት ወስጥ ዳግም ገብተው ይታያሉ ተብሎ ስለማይታሰብ በዕረፍቱ ቀናት የቡድናቸውን ትኩረት እና የጨዋታ ተነሳሽነት በእጅጉ አሻሽለው ለነገው ፍልሚያ እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።
መከላከያ ሙሉ ትኩረት ላይ ሆኖ በተመለከትንባቸው ጨዋታዎች ከነበሩት ጠንካራ ጎኖች ውስጥ የመከላከል ሽግግሩ በነገው ጨዋታ ጎልቶ ሊታይ ይችላል። በታታሪነት ወደ ኋላ በመሳብ በሜዳው ቁመት ኮሪደሮችን የመዝጋት ብቃት ያላቸው የመስመር አጥቂዎቹ እንዲሁም ከተከላካይ መስመሩ ፊት ተጋጣሚ ክፍተት እንዳያገኝ በትኩረት የሚሰራው ኢማኑኤል ላሪያ የሚኖራቸው አቋም ቡድኑ በቅዱስ ጊዮርጊስ አማካዮች ብልጫ እንዳይወሰድበት እገዛ ያደርግለታል። በሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ያስተናገደው የቅዱስ ጊዮርጊስ የመከላካል አደረጃጀትም አልፎ አልፎ ከሚታይበት መዘናጋት ውጪ ለክፉ የሚሰጥ አይደለም። ሆኖም ከእስካሁኖቹ ሦስት ተጋጣሚዎቹ ጋር ሲነፃፀር በመልሶ ማጥቃት ስል የሆነ ቡድንን የሚያገኝ በመሆኑ ነገ ከበድ ያለ ፈተና ሊያገኘው ይችላል።
ሁለቱ ቡድኖች የሚያጠቁባቸው መንገዶች ልዩነት ቢኖራቸውም መቋጫቸውን በአመዛኙ የፊት መስመር አጥቂያቸው ጋር ማድረጋቸው ያመሳስላቸዋል። የመከላከያው ጋናዊ አጥቂ ኢማኑኤል ኦኩቱ አርባምንጭን የረቱበትን ግብ ከማስቆጠሩ ባለፈ ቡድኑ ሁለተኛ ኳሶችን እንዲጠቀም ጉልበቱን እና ተክለሰውነቱን በመጠቀም እገዛ ሲያደርግ ይስተዋላል። የጊዮርጊሱ ቶጓዊ አጥቂ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮም ቡድኑ በቅብብሎች ሰብሮ መግባት ሲሳነው ረዘም ያሉ ኳሶች መዳረሻ ሲሆን ሁለት ግቦችም አሉት። ይህንን ስንመለከት የሁለቱ አጥቂዎች አበርክቶት በጨዋታው ላይ አንዳች ለውጥ ሊፈጥር እንደሚችል ያሳየናል።
በጨዋታው አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ተደጋጋሚ ስህተት የሰራው ግብ ጠባቂያቸውን ክሌመንት ቦዬን ጨምሮ በተለመደ ተቀያያሪ ሚና የመስጠት አካሄዳቸው በርከት ያሉ ለውጦች ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ከገናናው ረጋሳ ሁለት ቢጫ ካርድ ቅጣት ውጪ ሙሉ ቡድናቸው በመልካም ጤና ላይ መገኘቱ እና የቢኒያም በላይ ከጉዳት መመለስ ደግሞ አማራጫቸውን ያሰፋላቸዋል። ቡድናቸውን ከመሩበት የመጀመሪያው የሰበታ ጨዋታ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የቴክኒክ ቦታው ላይ እንደሚታዩ የሚጠበቁት ዝላትኮ ክራምፖቲች ግን በስብስባቸው ውስጥ የማያገኟቸው ተጫዋቾች ይኖራሉ። ወደ ልምምድ የተመለሰው አዲስ ግደይን ጨምሮ ጋቶች ፓኖም እና አማኑኤል ተርፉ በጉዳት ቸርነት ጉግሳ ደግሞ በቤተሰብ ጉዳይ ከቡድኑ ጋር አይገኙም። ከዚህ በተለየ ሳለሀዲን በርጌቾ እና ናትናኤል ዘለቀ ወደ ቡድኑ መመለሳቸው ተሰምቷል።
ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ የመሀል ዳኝነት የሚመራ ሲሆን የመግቢያ ትኬቱ ከ6 ሰዓት ጀምሮ በአርቴፊሻል ስታዲየም እና በፒና ሆቴል እንደሚሸጥ ታውቋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ አንጋፋ ክለቦች በሊጉ 28 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ አላቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ 12 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን በረጅም ርቀት ሲይዝ መከላከያ ሁለት ጊዜ ድል ቀንቶያል ፤ ቀሪ 14 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ። ቅዱስ ጊዮርጊስ 35 መከላከያ ደግሞ 16 ግቦችን ከመረብ አገናኝተዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
መከላከያ (4-2-3-1)
ሙሴ ገብረኪዳን
ልደቱ ጌታቸው – አሌክስ ተሰማ – ኢብራሂም ሁሴን – ዳዊት ማሞ
ኢማኑኤል ላሪያ – አዲሱ አቱላ
ሰመረ ሀፍተይ – ቢኒያም በላይ – ግሩም ሀጎስ
ኦኩቱ ኢማኑኤል
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)
ቻርለስ ሉኩዋጎ
ሱለይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ
ሀይደር ሸረፋ – በረከት ወልዴ
አቤል ያለው – ከነዓን ማርክነህ – ቡልቻ ሹራ
ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ