“መሥራት እየቻልኩ ከምወደው የዳኝነት ሙያ ራሴን አግልያለው” – ብሩክ የማነብርሀን

የቀድሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን ራሱን ከዳኝነት ለማግለል ያበቃውን ምክንያት ለሶከር ኢትዮጵያ አጋርቷል።

ያለፉትን ዓመታት ከመምርያ ጀምሮ ፌደራል በኃላም እስካለፈው የውድድር ዘመን ድረስ ለስምንት ዓመታት በኢንተርናሽናል ዳኝነት ያገለገለው ብሩክ የማነብርሀን ለ2022 ኢንተርናሽናል ዳኝነት ወደ ፊፋ ከተላኩ ዳኞች ዝርዝር ውስጥ ሳይካተት መቅረቱ ይታወሳል። አርቢቴር ብሩክ በተለያዮ ምክንያቶች ራሱን ከዳኝነት ማግለሉን እና ለዚህ ውሳኔ የደረሰበትን ምክንያት ለሶከር ኢትዮጵያ አስረድቷል። እኛም የእርሱን ቃል እንደወረደ እንደሚከተለው አቅርበናል።

“ወደ ዳኝነት ሙያ ከገባሁበት ጊዜ አንስቶ ሀገሬን በቅንነት በምችለው አቅም ሁሉ አገልግያለሁ። ለዚህም በተለያየ ጊዜ እውቅና እና የምስጉን ዳኝነትን ሽልማትን ተቀብያለሁ። አሁን የተወቀረው ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ከዚህ ቀደም ለአራት ዓመታት በሰራበት ጊዜ ኢንተርናሽናል ዳኛ እንዳልሆን ብዙ ጥረት አድርገዋል። ፈተናውን እያለፍኩ ስሜን ሳያስተላልፉልኝ ኢንተርናሽናል እንዳልሆን ጥረዋል። ሆኖም ያለውን ችግር ተቋቁሜ እነርሱ ከኃለፊነት ሲነሱ በአቅሜ ወደ ኢንተርናሽናል ዳኛ የመሆን ህልሜን አሳክቼ ሀገሬን በመወከል ስምንት ዓመት አገልግያለሁ።

“ከዚህ በፊት አላሰራ ይሉኝ የነበሩ ሰዎች በድጋሚ ወደዚህ ቦታ ተመልሰው ስለመጡ ከዓምና ጀምሮ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፌ ስሰራ ቆይቻለሁ። በተለይ ዓምና ብዙ ጨዋታዎችን በብቃት ዳኝቼ ሳበቃ የምስጉን ዳኝነትን ምርጫ ለሌላ ሰው በመስጠት በኔ ላይ የቆየ ጥላቻ እንዳላቸው አሳይተዋል።

“ዘንድሮም ሆን ብለው እኔን ለመጣል የተለያዩ ምክንያቶች በማቅረብ በተደጋጋሚ የአካል ብቃት ፈተናውን እየደጋገሙ እንዳላልፍ በማድረግ የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጄን ነጠቁኝ። ጊዜ ሁሉን ነገር እንዲፈርድ እየሰጠው እነዚህ ሰዎች ከዚህ በኃላ ሊያሰሩኝ እንደማይችል ስላመንኩ እና አብሬ መስራት ስላልፈለኩ ክብሬንም አሳልፌ መስጠት ስለማልፈልግ ያለኝን ክብር በመጠበቅ ዳኝነቱን ለማቆም ወስኛለው። ይህ ኮሚቴ እያለ ነገ ብሰራም እንኳን በሰበብ አስባቡ እንደሚቀጡኝ ስለማቅ መስራት እየቻልኩኝ ከምወደው ሙያ ክብሬን ጠብቄ ራሴን ከዳኝነቱን ለማቆም ተገድጃለው።

“ከዚህ በኃላ ግን ፌዴሬሽኑ በሚፈልገኝ ማንኛውም ሥራ በኮሚሽነርነትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ልምዴን በማካፈል ዳኞችን ለማብቃት በሚሰጡ ስልጠናዎች የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት ያለኝ መሆኑን እየገለፅኩ በዳኝነት ዘመኔ እኔን ላበቁኝ ኢንስትራክተሮች እንዲሁም ለሙያ አጋሮቼ ስለነበረን ነገር ሁሉ በጣም አመሰግናለው። ”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳኞች ከሚቴ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚለው ነገር ካለ ምላሻቸውን በቀጣይ ይዘን የምንቀርብ መሆኑን ለመጠቆም እንፈልጋለን።

ያጋሩ