ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የ4ኛ የጨዋታ ሳምንት ትኩረት የሳቡ የክለቦች ጉዳይ የመጀመሪያ ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 በጀብደኝነት የተሞላው የአርባምንጭ ከተማ የጨዋታ ዕቅድ

ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተመለሱት አርባምንጭ ከተማዎች በሊጉ የመጀመሪያ ሦስት ጨዋታዎች ሊተገብሩ ካሰቡት የጨዋታ መንገድ በተወሰነ መልኩ የተለወጠ አቀራረብን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አስመልክተውናል።

በሦስቱ ጨዋታዎች አርባምንጮች ጥንቃቄ ባስቀደመ መንገድ በቁጥር በርከት ብለው ወደ ራሳቸው ሜዳ ተሰብስበው በመከላከል እና ኳሶችን በሚያገኙበት ወቅት ደግሞ ይበልጥ በቀጥተኝነት አጥቂዎችን ተደራሽ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም እንዲሁም ከመስመሮች በሚሻገሩ ኳሶች አደጋዎችን ለመፍጠር ሲታትሩ ያስተዋል ነበር።

ቡድኑ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን በሤስቱ ጨዋታዎች ያልተሸነፈውን ባህርዳር ከተማን በአስገራሚ መልኩ 2-1 በሆነ ውጤት ሲረታ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በቅድመ ጨዋታ ቃለመጠይቃቸው እንደገለፁት ከተለመደው አቀራረባቸው የተለየ እና በጀብደኝነት በቁጥር በርከት በማለት በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ ኳሶችን ለመንጠቅ የሚፈልግ ቡድን ሆኖ ተመልክተነዋል።

በጨዋታው አርባምንጭ ከተማዎች አራት የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾቻቸውን ወደ መሀል ሜዳ አስጠግተው የተቀሩትን ስድስት የሜዳ ላይ ተጫዋቾችን ደግሞ ከፍ ብለው በላቀ ትጋት የባህርዳር ከተማ ተጫዋቾችን ጫና ውስጥ በመክተት ባህርዳሮች በነፃነት ኳሶችን ጀምረው ከራሳቸው ሜዳ እንዳይወጡ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ነበሩ። ከዚህም ባለፈ በፈጠሩት ጫና መነሻነት የተጋጣሚ ተጫዋቾችን ስህተት ውስጥ በመክተት በተደጋጋሚ ኳሶችን በሜዳው የላይኛው ክፍል ቢያገኙም በተጫዋቾች ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ የተነሳ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

እርግጥ በጫና መጫወት ከአካላዊ ዝግጅት ባለፈ ከፍተኛ የአዕምሮ ዝግጅት እንደሚፈልግ ይታወቃል። የአርባምንጭ ከተማ ተጫዋቾችም በአዕምሮ ደረጃ አንድ ተጫዋች ጫና ለመፍጠር ሩጫ አድርጎ ቢታለፍም ከጀርባው ሌሎች የቡድኑ አጋሮቹ ጫና ለመፍጠር ዝግጁ መሆናቸውን በማመመን ያሳዩት በመጠኑም ቢሆን ቅርፅ ያለው የጫና መፍጠር እንቅስቃሴ ጥሩ የሚባል ነበር።

ነገርግን በባህርዳሩ ጨዋታ የታዘብነው ሌላኛው ጉዳይ አርባምንጭ ከተማዎች መች እና እንዴት ጫና መፍጠር እንዳለባቸው በቅጡ የተረዱ አይመስልም። ምናልባት የጨዋታ ዕቅዳቸው በዚህ መልኩ የተቃኘ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ባንችልም በጨዋታው የአርባምንጭ ተጫዋቾች እያንዳንዱን የተጋጣሚ ቅብብሎሾችን ለማቋረጥ ሲውተረተሩ ተስውሏል።

ይህ ጨዋታ ከቀናት ዕረፍት በኋላ ሊጉ ዳግም የጀመረበት እንደመሆኑ ተጫዋቾች ከዕረፍት መልስ በሙሉ ጉልበት እንደመገኘታቸው ብዙም አካላዊ ጫናውን ባያስተውሉትም በመሰል የጨዋታ መንገድ ለመቀጠል የሚያልሙ ከሆነ ግን መች እና እንዴት የሚለው ጉዳይ ወሳኝነታቸው የጎላ ይሆናል። በቀጣይነት ይህን መንገድ ለማስቀጠል የተጫዋቾችን ጉልበት በተጠና መልኩ በቁጠባ መጠቀም እጅግ ወሳኝነት አለው።

በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከመሮጥ ይልቅ በተጠና መልኩ እንደ ተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ሁኔታ ፣ እንደ ጨዋታ መንገዳቸው እና ሌሎች ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ ከጨዋታ ጨዋታ የሚለዋወጥ የጫና መቀስቀሻ (Pressing Trigger) በመጠቀም በተወሰነ መልኩ የተጠናን መንገድ መከተል የግድ የሚል ይሆናል። በተጨማሪም ጫና ፈጥሮ መጫወት ማለት በቁጥር በርከት ብሎ ኳስ የያዘውን ሰው ከመክበብ ባለፈ በተቀናጀ መልኩ ኳሱን ለመንጠቅ የሚንቀሳቀሰው ቡድን ከተጋጣሚ አቋቋም ፣ ከኳሱ እና ከተያያዥ ጉዳዮች መነሻነት የሚቃኝ የቦታ አያያዝ ለመከተል የማይሞክሩ ከሆነ እና እንደው እንደነገሩ በደመነፍስ ኳስ የያዘው ሰው ለመክበብ በሚደረገው ጥረት ኳሱን የያዘው ተጫዋች በዚህ ከበባ ውስጥ ሆኖ ሌላ የቡድን አጋሩን የሚያገኝበት ዕድል ከተፈጠረ በቁጥር በርከት ያለ ተጫዋቾች በአንድ ኳስ የሚቆረጡ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ አደጋ መደቀኑ የሚቀር አይደለም። ስለዚህ በጥቂቱም ቢሆን ከላይ የጠቀስናቸው ሀሳቦች የጨዋታ መንገዱን ለማሳደግ ትኩረት የሚሹ ናቸው።

አሰልጣኙም በድህረ ጨዋታ ቃለመጠይቃቸው ወቅት ቡድናቸው እሳቸው ወደሚፈልጉት የጨዋታ መንገድ እየመጣ ስለመሆኑ መናገራቸው በቀጣይ ጨዋታዎች ይህን ጫና ፈጥሮ የመጫወትን ነገር የሚያስቀጥሉ ይመስላል። በንፅፅር የተሻለ የስብስብ ጥራት ካለው ባህርዳር ከተማ ጋር በድፍረት በዚህ ጀብጀኝነት በተሞላበት አቀራረብ ገብተው ውጤት አስመዝግበው የመውጣታቸው ነገር ግን አድናቆት የሚቸረው ነው።

👉 ቀና እያለ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ

በሊጉ ሁለት የመክፈቻ ጨዋታዎች እጅግ ደካማ ከሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር ሽንፈቶችን አስተናግደው የነበሩት አዲስአበባ ከተማዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ግን መከላከያን እንዲሁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ የአምና የሊጉ አሸናፊዎቹን ፋሲል ከነማን በማሸነፍ ከዘመመው አጀማመራቸው በተወሰነ መልኩ ቀና እያሉ ይገኛል።

በፋሲሉ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማዎች የነበራቸው ከፍተኛ የፍላጎት እና የተነሳሽነት ስሜት በጨዋታው ልዩነት የፈጠረ ነገር ነበር። ከምንም በላይ መታተር፣ ተስፋ አለመቁረጥ፣ ተጋጣሚን በወሳኝ የሜዳ ክፍሎች ከኳስ ጋር ጊዜ አለመስጠት እና ፍጥነት ጨዋታውን በመጀመሪያው አጋማሽ እንዲያገባድዱት ያደረጉ ምክንያቶች ነበሩ። እንደውም በግብ ዘቡ ሳማኪ የግል ጥረት እና በራሳቸው አጥቂዎች ስል አለመሆን መረብ ላይ ያላረፉ ኳሶች ነበሩ እንጂ መሪነታቸውን አስፍተው ወደ መልበሻ ክፍል የሚያመሩበት ሁነት ከአንድም ሦስት ጊዜ ተፈጥሮ ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ ልዩ የነበሩት አዲስ አበባዎች ፋሲሎች ኳስ እንዲመሰርቱ ከፈቀዱላቸው በኋላ በሁለተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ግን በቁጥር በርከት ብለው የመቀባበያ አማራጮቻቸውን እየዘጉ ለስህተት እየዳረጉዋቸው ታይቷል። በመሐል ሜዳ የተቀበሉትን ኳስ ደግሞ በፈጣን ሽግግር ወደ ሳጥን በመውሰድ ለግብነት ሲሞክሩት ነበር። በጨዋታው ፋሲሎች ይህንን ፈጣን የአዲስ አበባዎች ሽግግር በሚገባ የሚያቆምላቸው የተከላካይ አማካይ ባለማግኘታቸውም ተከላካዮቻቸው ሲጋለጡ ተስተውሏል። ከምንም በላይ ደግሞ ከመስመር አጥቂዎቹ ፍፁም እና እንዳለ ፍጥነት በተጨማሪ የአማካይ እና የአጥቂ መስመሩን በሚገባ ሲያገናኝ የነበረው ኤሊያስ አህመድ ከ9 ቁጥር አጥቂው ሪችሞንድ አዶንጎ ጋር የነበረውን ጥምረት ፋሲሎች መመከት ባለመቻላቸው ሲፈተኑ ነበር።

በማጥቃቱ ብቻ ሳይሆን በመከላከሉም ረገድ የተዋጣላቸው የነበሩት አዲስ አበባዎች የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ እና የደረጃ ሰንጠረዡ መሪ በጨዋታው ከአንድ ያልበለጠ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ እንዳያደርግ የዘየዱበት መንገድ የሚደነቅ ነው። እርግጥ የፋሲል ከነማዎች የማጥቃት ኃይል በጨዋታው እጅግ ወርዶ ቢታይም ወሳኞቹን ተጫዋቾች ከእንቅስቃሴ ውጪ ለማድረግ የነበራቸው የግል እና ቡድናዊ የመከላከል መዋቅር ጠንካራ ነበር። ይህ መዋቅር በሁለተኛው አጋማሽ በተወሰነ ቢፈተንም ጫናዎችን ተቋቁሞ መውጣቱ ጭብጨባ የሚያስቸረው ነው።

አንዳንድ ጊዜ የጨዋታዎች ውጤት በተጋጣሚ ቡድኖች መካከል ባለ የተጫዋቾች የጥራት ልዩነት (Quality Disparity) ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በጨዋታ ዕቅድ እንዲሁም በሜዳ ላይ በተሻለ ፍላጎት ያለውን ሁሉ ሜዳ ላይ ለመስጠት የተዘጋጀው ማነው የሚለው ጉዳይ የጨዋታዎችን ውጤት የመወሰን አቅሙ ከፍ ያለ ነው።

በፋሲል እና በአዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ሜዳ ላይ ከነበሩ ቴክኒካዊ እና ታክቲካዊ ጉዳዮች ባለፈ አዕምሯዊ ጉዳዮች ልዩነት ፈጥረው የተመለከትንበት ጨዋታ ነበር።

👉 ውጤት ተኮሩ ወላይታ ድቻ

የየትኛውም ቡድን ደጋፊዎች ቡድናቸው አዘናንቶ ቢያሸንፍ ምርጫቸው ነው። ነገር ግን ከምንም በላይ አሸናፊ መሆኑ የበለጠ ዋጋ ይሰጠዋል። አዝናንቶ ማሸነፍ የሚለው አባባል በራሱ አከራካሪ ትርጓሚ ቢኖረውም ይበልጥ እዞራሱን ገልፆ ወይንም በአዎንታዊ አጨዋወት ማሸነፍ በሚለው ትርጓሚ እንኳን ብንወስደው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በወላይታ ድቻ እየገነቡት የሚገኘው ቡድን ግን እርሳቸውም እንደሚሉት በየትኛውም መንገድ ማሸነፍን ምርጫው ያደረገ ሆኖ ተመልከተናዋል።

ሊጉን በሽንፈት የጀመረው ወላይታ ድቻ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን መርታቱን ተከትሎ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል። በሦስቱም ድል ባደረገባቸው ጨዋታዎች በአመዛኙ ወደ ራሱ ሜዳ ሰብሰብ ብሎ በመጫወት ተጋጣሚዎቹን በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች ለመጉዳት የሚጥር ቡድን እንደሆነ ተመልክተናል። ይህም አጨዋወት ቡድኑ ባሸነፈባቸው የሀዋሳ ፣ አዳማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታዎች በደንብ ቁልጭ ብሎ የተስተዋለ እውነታ ነው።

ወላይታ ድቻ በ2006 የውድድር ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ካደገበት ጊዜ አንስቶ ላለመሸነፍ ቅድሚያን በሚሰጥ አጨዋወት በመከላከሉ በጣም ጠጣር የሆነ እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት የጨዋታ ውጤቶችን ለመወሰን የሚፈልግ ቡድን እንደሆነ ይታወቃል። ቡድኑን እርግጥ እግርኳሳዊ ማንነት ለማለት ቢከብድም ከዚህ የአጨዋወት መንገድ ወጣ ብሎ በተወሰነ መልኩ ኳስ ቁጥጥር ላይ ያተኮረ ቡድን ለመሆን በሞከራባቸው ወቅቶች ቡድኑ ምን ያህል በብዙ መንገድ እንደተቸገረ ተመልክተናል። አምናም አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ቡድን ተረክበው ቡድኑን ወደ መሰረታዊው ነገር እንዲመልስ በማስቻላቸው ከመውረድ ስጋት ተላቆ በሊጉ የተረጋጋ ስፍራን ይዞ ለማጠናቀቅ ችሏል።

ዘንድሮም በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እየተመራ የሚገኘው ድቻ የቡድኑን መሰረታዊ እሴቶችን በሚገባ ሜዳ ላይ እያስመለከተ በውጤት በማጀብ አሁን በሰንጠረዡ አናት ከፋሲል ከነማ ጋር በነጥብ በመስተካከል በሊጉ በሁለተኛ ደረጃ ለመቀመጥ በቅተዋል።

👉 ኢትዮጵያ ቡና ከህመሙ አልዳነም

አምና ሊጉን በሁለተኝነት በማጠናቀቅ በአፍሪካ መድረክ ተሳትፎን ማረጋገጥ ችለው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች የዘንድሮ አጀማመራቸው መልካም የሚባል አልሆነላቸውም። ከአራት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ቡድኑ ምንም ጨዋታ ማሸነፍ ሳይችል በሁለት ነጥብ እና በአምስት የግብ ዕዳ በሊጉ ሰንጠረዥ 15ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል።

ቡድኑ በአራቱ የሊግ ጨዋታዎች በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ነገሮች መልክ የያዙለት አይመስልም። በአራቱ ጨዋታዎች አቡበከር ናስርን የያዘው የአጥቂ መስመራቸው እስካሁን ሁለት ግቦችን ብቻ ሲሆን ያስቆጠረው በተቃራኒው መረጋጋት የተሳነው የቡድኑ መከላከል ሰባት ግቦችን አስተናግዷል።

ውጤትን መሰረት ያደረጉ ትንታኔዎች አብዛኛውን ጊዜ ሜዳ ላይ ያለውን የቡድኑን እውነታ ባይገልፁም ከውጤት ባለፈ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቡድኑን የምንመዝነው ከሆነ ግን ብቸኛው አዎንታዊ ነገር በዚህ የውጤት ማጣት ውስጥም ቢሆን ቡድን ያዋጣኛል ባለው መንገድ ፀንቶ የመጓዙ ነገር ብቻ ነው። ከዛ ባለፈ ግን ቡድኑ አምና ውጤታማ ያደረገውን የጨዋታ መንገድን በመከላከሉ ሆነ በማጥቃቱ ረገድ በጥራት ሜዳ ላይ ለመተግበር ሲቸገር እያስተዋልን እንገኛለን።

በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት እንደ ኢትዮጵያ ቡና ሁሉ ደካማ የሊግ ጅማሮ ያደረገው እና እስካሁን ምንም ነጥብ ማስመዝገብ ያልቻለውን ጅማ አባ ጅፋርን በሚገጥምበት ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ሆኖ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።

👉 በመጨረሻም ጅማ አባ ጅፋር አስቆጥሯል

በአዲሱ የውድድር ዘመን በመጀመሪያዎቹ ሦስት የጨዋታ ሳምንታት ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው የነበሩት ጅማ አባ ጅፋሮች በሊጉ ከ355 የጨዋታ ደቂቃዎች በኋላ በኢዳላሚን ናስር አማካኝነት የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ግባቸውን ማስቆጠር ችለዋል።

በሊጉ የአራት ሳምንታት ጉዞ በርካታ ግቦችን (9) ያስተናገደው ቡድኑ ያልተሟላ የተጫዋቾች ስብስብን ይዞ እንደመጀመሩ ከሰሞኑ በነበረው የዕረፍት ጊዜ ተስፈኛ ተጫዋቾችን የሙከራ ጊዜ በመስጠት ማሳመን የቻሉትን ቢጫ ቴሴራ እና በውሰት ውል ወደ ስብስቡ የቀላቀለበትን ሂደት ተመልክተናል። ወደ ስብስቡ ከቀላቀላቸው ተጫዋቾች መካከል ግብጠባቂውን አላዛር ማርቆስ ጨምሮ ሙሴ ከበላ ፣ ብሩክ አለማየሁ እና ትንሳኤ ያብጌታን የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታቸውን ባደረጉበት የድሬዳዋ ከተማው ጨዋታ አሁን በሊጉ ከሚገኙ የተቀሩት ቡድኖች በተወሰነ ርቀት ወደ ኋላ እንደቀሩ በግልፅ በሚታይ መልኩ ይህ ነው የሚባል የመከላከልም ሆነ የማጥቃት ቅርፅ አልባ ቡድን እንደሆነ ተመልክተናል።

አምናም በተመሳሳይ ወቅት ሊጉ ከአራተኛ የጨዋታ ሳምንት መጠናቀቅ በኋላ ጅማ አባ ጅፋር በአንድ ነጥብ እና በስምንት የግብ ዕዳ የሊጉ ግርጌ ላይ የነበረ ሲሆን ዘንድሮም ቡድኑ ከአምናው ስህተቱ ብዙም የተማረ አይመስልም። ውድድሩ ገና መጀመሩ ቢሆንም ከወዲሁ ነጥቦችን መጣል ግን በተለይ በሁለተኛው ዙር ውድድሩ ከረር እያለ በሚመጣበት ወቅት ቡድኑን ዋጋ እንዳያስከፍለው ያሰጋል። በመሆኑም ነገሮች በፍጥነት መስተካከል ካልጀመሩ ከ2010 የሊግ ክብር በኋላ እየተንገዳገደ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር የሊጉ ቆይታውን ለማረጋገጥ የሚቸገር ይመስላል።

ያጋሩ