የ2013 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ኮከቦች ታውቀዋል

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሥር ከሚደረጉ ውድድሮች መካከል አንዱ ሁለተኛው የሀገሪቱ የሊግ እርከን የሆነው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ነው። 33 ክለቦች በሦስት ምድብ ተከፋፍለው ባደረጓቸው ጨዋታዎችም አዲስ አበባ ከተማ፣ መከላከያ እና አርባምንጭ ከተማ የየምድቦቹ የበላይ ሆነው ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጋቸው ይታወሳል።

የውድድሩ የበላይ አካል የሆነው ፌዴሬሽን በአሁኑ ሰዓት የዘንድሮውን የውድድር ዓመት የእጣ ማውጣት እና የደንብ ውይይት መርሐ-ግብር በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን የባለፈው ዓመት ሪፖርት ሲቀርብም የየምድቦቹ ኮከቦች ይፋ ሆነዋል።

ዘጠኝ ክለቦች በነበሩበት ምድብ አንድ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ፀጋ ደርቤ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ሲመረጥ የመከላከያው ጀፋር ደሊል ደግሞ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኗል። በምድቡ 38 ነጥቦችን በመሰብሰብ ክለባቸው መከላከያን ወደ ሊጉ ያሳደጉት ዮሐንስ ሳህሌ ደግሞ ኮከብ አሠልጣኝ ሆነው ተመርጠዋል።

በምድብ ሁለት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማው አቡበከር ወንድሙ ኮከብ ተጫዋች ሲባል የቡድን አጋሩ የነበረው ሳምሶን አሰፋም ኮከብ የግብ ዘብ ሆኗል። እንደ አሠልጣኝ ዮሐንስ አዲስ አበባን ወደ ሊጉ ያሳደጉት እስማኤል አቡበከር ደግሞ ኮከብ አሠልጣኝ ተብለው ተመርጠዋል።

በመጨረሻው ምድብ ደግሞ የአርባምንጩ ፍቃዱ መኮንን ኮከብ ሲባል የኮልፌ ቀራኒዮው የግብ ዘብ ሀይማኖት አዲሱ በበኩሉ የምድቡ ጠንካራ ግብ ጠባቂ በመባል በኮከብነት ተመርጧል። የዚህ ምድብም ኮከብ አሠልጣኝ አርባምንጭን ወደ ሊጉ የመለሱት አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ ሆነዋል።

በተያያዘ በምድብ አንድ ሚካኤል ጣዕመ እና አብይ አበበ፣ በምድብ ሁለት በሪሶ ወላንጎ እና ቢቂላ ሁንዴሳ እንዲሁም በምድብ ሦስት ሄኖክ አበበ እና ደስታ ጉራቻ ምስጉን ዋና እና ረዳት ዳኞች በመሆን ተመርጠዋል። ከዚህ ውጪ ፌዴራል ፖሊስ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና ጌዲዮ ዲላ በሦስቱ ምድቦች የስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊዎች ተብለው መመረጣቸው ታውቋል።

የምድቦቹ የኮከቦቹ ምርጫ ዝርዝር ይፋ ይሁን እንጂ ፌዴሬሽኑ ወደፊት በሚገለፅ ቀን ኮከብ ተብለው ለተመረጡት አካላት በአንድ በተመረጠ ቦታ የሽልማታ ሥነ ስርዓት እንደሚያደርግ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሞ አባል እና የከፍተኛ ሊግ ሰብሳቢ አቶ አሊቢራህ መሐመድ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።