ሪፖርት | ከቆመ ኳስ የተገኙ ሁለት ጎሎች ሲዳማ እና ሰበታን ነጥብ አጋርተዋል

በሦስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር በሀዋሳ ከተማ የተረቱት ሲዳማ ቡናዎች ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ጨዋታ ተስፋዬ በቀለን በጊት ጋትጉት፣ ብርሃኑ አሻሞ በሙሉዓለም መስፍን፣ ብሩክ ሙሉጌታ በዳዊት ተፈራ እንዲሁም ፍራንሲስ ካሀታ በሀብታሙ ገዛኸኝ ለውጠው ጨዋታውን ቀርበዋል። ተጋባዦቹ ሰበታ ከተማዎች ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ፍልሚያ ሦስት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ወልደአማኑኤል ጌቱ በቢያድግልኝ ኤሊያስ፣ ክሪዚስቶም ንታንቢ በዮናስ አቡሌ እንዲሁም ዱሬሳ ሹቢሳ በዘላለም ኢሳይያስ ተለውጠዋል።

ገና ጨዋታው እንደተጀመረ የመዓዘን ምት ያገኙት ሲዳማ ቡናዎች ሰለሞን ሀብቴ አሻምቶት ጊት ጋትኩት በግንባሩ በሞከረው ኳስ በጊዜ መሪ ሊሆኑ ነበር። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሰበታዎች ዮናስ አቡሌ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ በግራ እግሩ ግብ ለማድረግ ጥሮ ነበር። በ13ኛው ደቂቃ ደግሞ የሲዳማ የመሐል ተከላካይ ጊት ጋትኩት የተሳሳተውን ኳስ ዘካሪያስ ፍቅሬ ደርሶበት ለመጠቀም ቢጥርም የግብ ዘቡ ተክለማርያም ሻንቆ እምብዛም ሳይቸገር ኳሱ ተቆጣጥሮታል። ከኳስ ውጪ አብዛኛውን እንቅስቃሴ ማድረግ የቀጠሉት ሰበታዎች የሲዳማን የመስመር ላይ ጥቃት ለመመከት ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው መጫወት ይዘዋል።

በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ሲዳማዎች ደግሞ በ23ኛው ደቂቃ ሌላ ጥቃት ፈፅመዋል። በዚህም ቴዎድሮስ ታፈሰ ከመሐል ሜዳ የላከውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን በግንባሩ ለመጠቀም ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። ከዚህ ሙከራ 10 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት በማድረግ እጅግ የሰላ ጥቃት ተጫዋቹ ሰንዝሯል። በተጠቀሰው ደቂቃ ይገዙ ቦጋለ ረጅም ርቀት ሮጦ ያገኘውን ኳስ ወደ ሳጥን ሲልከው ፍሬው አግኝቶ ወደ ግብ መትቶት የነበረ ቢሆንም ኳስ ወደ ላይ ተነስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። ጥሩ ፉክክር ማሳየት በመቀጠልም በ35ኛው ደቂቃ ጁኒያንስ ናንጄቤ ከቀኝ መስመር የደረሰውን ኳስ በሞከረው አጋጣሚ ጨዋታው ግብ ሊያገኝ ነበር። በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎች ግን ሌላ ሙከራ ሳይደረግ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

 

በጨዋታው የተሻለ የማጥቃት ተነሳሽነት የነበራቸው ሲዳማዎች አጋማሹ እንደተጀመረ መሪ ሆነዋል። በዚህም በ49ኛው ደቂቃ ሰለሞን ሀብቴ ወደ ቀኝ ካዘነበለ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ ሲመታው ሀብታሙ ገዛኸኝ በግንባሩ በትንሹ ጨርፎት ኳስ እና መረብ ተገናኝቷል። በጊዜ መሪነት የተወሰደባቸው ሰበታዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ሳሙኤል ሳሊሶ ከቅጣት አሻምቶት በረከት ሳሙኤል በሞከረው ኳስ ሊያገኙ ነበር። በ62ኛው ደቂቃ ደግሞ በተቃራኒ ቦታ የተገኘን የቅጣት ምት በድጋሜ ሳሙኤል ለመጠቀም ዳድቶ ቡድኑን አቻ ሊያደርግ ነበር።

በሀይሉ ግርማ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ ሌላ የቅጣት ምት በ75ኛው ደቂቃ ያገኙት ሰበታ ከተማዎች በጥቂት የደቂቃ ልዩነት ካገኟቸው ሦስት የቅጣት ምቶች የመጨረሻውን ግብ አድርገውታል። በዚህም በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ዘካሪያስ ፍቅሬን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ፍፁም ገብረማርያም ከኃይለሚካኤል አደፍርስ የተሻገረውን የቅጣት ምት በሩቁ ቋሚ ሆኖ በመጠበቅ በግንባሩ አስቆጥሮታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ወደ መሪነት የሚሄዱበትብ ኳስ በዮናስ አቡሌ የግንባር ኳስ ሊያገኙ የነበረ ቢሆንም ውጥናቸውን የግቡ አግዳሚ አምክኖባቸዋል። በቀሪ ደቂቃዎችም ሰበታዎች በተነቃቃ ሁኔታ ማጥቃቱ ላይ ተጠምደው ቢያሳልፉም ተጨማሪ ግብ አላገኙም። ሲዳማዎች ግን ከደቂቃ ደቂቃ እየወረዱ መጥተው በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ ይዘው ሳይወጡ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ከዛሬው ውጤት በኋላ ሲዳማ ቡና ከ12ኛ ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሰበታ ከተማ ደግሞ ባለበት 13ተኛ ደረጃ ተቀምጧል።