ከዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የተደረጋው የአሰልጣኞች እና የሱፐር ስፖርት ቆይታ ይህንን ይመስላል።
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና
ጨዋታው ‘ውጤቱ ያስፈልገናል’ ከማለታቸው አንፃር
በዛ ስሜት ውስጥ ሆነን ነው የመራነው። ግን ጫና ውስጥ ገብተህ ስትጫወት ትንሽ ያስቸግራል። በእኛ እንቅስቃሴ በኩል ላለመሸነፍ ወይንም ነጥብ ላለመጋራት ብዙ ጥፋቶች ይሰሩ ነበር። አትስሩ ብንላቸውም ተመልሰው ወደዛ ነገር ይገቡ ነበር። ያ ጫናው የፈጠረው ነገር ነው። ትዕግስት ይፈልጋል ኳስ ፤ የሂደት ጉዳይ ነው። በዚህ ሦስት እና አራት ጨዋታዎች ጫና ውስጥ የገቡ ይመስለኛል ሳስበው። ለዛ ነው እንጂ ነጥብ የተጋራነው ማሸነፍ ይገባን ነበር።
በቆሙ ኳሶች ጎሎች ስለመቀጠራቸው
በዓለም ላይም ሰላሳ ከመቶው በቆሙ ካሶች ጎል ይቆጠራል። ከዚህ አንፃር ውጤታማ ነበር ማለት ነው። ለዚህም ነው ጥንቃቄ እንውሰድ ያልነው። በተደጋጋሚ በጫና ውስጥ ሆነህ ስትጫወት ተደጋጋሚ ጥፋቶች ትሰራለህ። ይዞት የሚመጣውም ነገር አለ።
ቡድኑ ስላሻሻላቸው ነገሮች
ተሻሽሏል ማለት አይቻልም። ሁል ጊዜ ጫና ውስጥ ስትገባ በፊት የምታደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ ታጣለህ። ስለዚህ አሁንም ከጫናው ለመውጣት ደጋፊዎቻችን ከጎናችን መሆን አለባቸው ብዬ አስባለሁ። ስህተቶች ያጋጥማሉ ለማረም በዚህ መልኩ አይደለም። የሰው ስም እየተጠራ ምናምን አይደለም።
በሳምንቱ ያልተጠበቁ ውጤቶች ስለመመዝገባቸው
ሁሉም በተመሳሳይ ደረጃ ላይ እንዳለ ያሳያል። ሁለተኛ የሥነ ልቦና ጉዳይም አለ። ካለፈው ልምድ እንደማውቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ተጫዋቾች ሲያሸንፉ የመኩራራት ነገር አለ። ነገ ደግሞ ሌላ ነገር ይሆናል። ተሸንፎ የመጣው ደግሞ ያለውን ኃይል በሙሉ አሰባስቦ ይመጣል። በቀጣይ ደግሞ ሌላ ይሆናል። እና ወጥነት የለውም። የሥነ ልቦና ሥራ መሰራት እንዳለበት ነው የሚያሳየው።
ፍሬው ሰለሞን ከብሔራዊ ቡድን መልስ ስላሳየው አቋም
ጥሩ ነው ፤ ፍሬው ያለፉትን ጨዋታዎች ሁሉ ጥሩ ነው። መመረጡም ተገቢ ነው። ከብሔራዊ ቡድን መልስም ጥሩ ነው የተንቀሳቀሰው። ሊበረታታ ይገባል።
አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ሰበታ ከተማ
ስለጨዋታው
እነሱም ለማሸነፍ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ፤ ጨዋታው ክፍት ነው። ታክቲካሊ የመታሰር ነገር አልነበረውም። ምክንያቱም ለማሸነፍ ስለነበር ፍላጎታችን በእነሱም በኩል ያ ስለነበር ውጥረት ነበረበት።
ጎሎች ከቆመ ኳስ ስለመቆጠራቸው
ፍፁም ያገባው ኳስ ጥሩ ነው። ግን ከዛ በፊትም ያገኘናቸው ኳሶች መጠቀም አለመቻላችን አንድ ነገር ነው። ከዛ ውጪ በእኛ በኩል የተከላካዩ ሁኔታ ጥብቅ ነው የነበረው። ግን ለስህተት ቅርብ ስትሆን ተደጋጋሚ ቅጣት ምቶች ይገኛሉ። እንደተገኙት ያለመጠቀም ግን ችግር ነበር።
ቡድኑ ውስጥ ስላለው መሻሻል
የተሻሻለው ከፍተኛ የሆነ የማሸነፍ ፍላጎት በመኖሩ ነው። በዛው ልክ ደግሞ ያልተሻሻለው ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች መጨረስ አሁንም ይቀረዋል የሚል ዖምነት አለኝ።
በሳምንቱ ስለመተዘገቡ ያልተጠበቁ ውጤቶች
የእኛ ሊግ የሚያስቸግር ይመስለኛል። ምክንያቱም ያልተገመቱ ቡድኖች ዓለም ላይም አንዳንዴ ነው የሚከሰቱት። እዚህ ግን በተደጋጋሚ እየተከሰተ ነው ያለው። ይሄ ለተመልካች ጥሩ ነው። እንደኛ ሆነህ ስታየው ደግሞ ሁል ጊዜም በተጠንቀቅ መቆም እንዳለብን የሚያሳይ ነው። ምክንያቱም ማን ይጥላል ፣ ማን ያሸንፋል የሚለው ግምት የተፋለሰበት ውድድር ነው።