ከተከታታይ ሁለት ድል በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ሦስት ለምንም ተረተው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት መከላከያዎች በቅጣት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ የሆነው ገናናው ረጋሳን ጨምሮ ሰመረ ሀፍታይ እና ልደቱ ጌታቸውን በአለምአንተ ካሳ፣ ቢኒያም በላይ እና ብሩክ ሰሙ ለውጠዋል። በሦስተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ በቤተሰብ ሀዘን ምክንያት ከስብስቡ ውጪ የሆነው ቸርነት ጉግሳን በሱሌይማን ሀሚድ፣ እስማኤል ኦሮ-አጎሮን በአማኑኤል ገብረሚካኤል እንዲሁም ደስታ ደሙን በከነዓን ማርክነህ ተክተዋል።
ጥሩ ፍክክር ገና ከጅማሮው ማሳየት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስን መሪ ሊያደርግ ነበር። በዚህም በሁለተኛው ደቂቃ አቤል ያለው ራሱን ነፃ አድርጎ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሲመታው ከነዓን ማርክነህ ተንሸራቶ ለመጠቀም ቢጥርም ሳይሳካለት ቀርቷል። በድጋሜ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ለመጠቀም ጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ ሊያደርግ ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጫናዎች የበዛባቸው መከላከያዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተር ይዘዋል። በዚህም በጨዋታው ሩብ ደቂቃ ቢኒያም በላይ ከወደ ግራ የሳጥኑ ክፍል ያገኘውን ኳስ በቀጥታ በመምታት ቻርለስ ሉክዋጎን ፈትኖ ነበር።
አሁንም የጊዮርጊስን የግብ ክልል መጎብኘት ያላቆሙት መከላከያዎች ከነዓን ማርክነህ ቢኒያም በላይ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ዓለምአንተ ካሳ ሲያሻማው ቁመታሙ አጥቂ ኦኩቱ ኢማኑኤል አግኝቶት ከመረብ ጋር ሊያዋህደው ነበር። ይሁ አጥቂ በ24ኛው ደቂቃ ደግሞ በተከላካዮች መሐል በመሮጥ ሌላ ኳስ ለመጠቀም ጥሩ ቻርለስ ሉክዋጎ አምክኖበታል። በቀጣይ የጨዋታው ደቂቃዎች የተመጣጠነ እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን በ35ኛው ደቂቃ ግን እጅግ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ተፈጥሯል። በዚህም ክሌመንት ቦየ በረጅሙ የላከውን ኳስ ግሩም ሀጎስ ፈጥኖ በመሮጥ ወደ ግብ ቢመታውም ሉክዋጎ በጥሩ ቅልጥፍና አድኖታል። አጀማመራቸው ጥሩ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጨረሻው የአጋማሹ ደቂቃ (43ኛው ደቂቃ) ከነዓን የግራ የሳጥኑ ክፍል ላይ በመገኘት በመታው ኳስ ሙከራ ቢያደርጉም የግቡ ቋሚ መልሶባቸዋል። የዕለቱ ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ፊሽካ ሊነፉ ሲሉ ደግሞ ጊዮርጊስ በተገኘ የቅጣት ምት እና የግብ ዘቡ ክሌመንት ተሳስቶ በነበረው ኳስ በድጋሜ የግብ ጫፍ ደርሰው ነበር።
በአንፃራዊነት ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እስከ 63ኛው ደቂቃ ድረስ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳይደረግበት ቀጥሏል። እርግጥ ቡድኖቹ የማጥቃት ሀይላቸውን ለማሻሻል የተጫዋቾች ለውጦችን ቢያደርጉም እምብዛም ውጤታማ ሲሆኑ አልታየም። ከላይ በተጠቀሰው ደቂቃ ግን በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ቡልቻ ሹራን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው እስማኤል ኦውሮ-አጎሮ በግራ እግሩ ሞክሮ ኳስ መትቶ ነበር። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ከነዓን የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ኳስ ለማግባት ቢጥርም የመከላከያው አምበል አሌክስ ተሰማ ኳሱን በሚገባ ተከላክሎት ከግብነት ታድጎታል።
በዚህኛው አጋማሽ እጅግ የተሻሻሉት ፈረሰኞቹ ትዕግስት ከተሞላበት አጨዋወት በኋላ በ77 እና 78ኛው ደቂቃ ሌላ መሪ የሚያደርጋቸውን አጋጣሚዎች ፈጥረው ነበር። በቅድሚያ ከነዓን ከያብስራ የደረሰውን ኳስ በቀጥታ መትቶት ክሌመንት ሲያድንበት በመቀጠል ደግሞ ኦውሮ-አጎሮ ተገኑ የሰጠውን ኳስ በግራ እግሩ ግብ ሊያደርገው ጥሮ መክኖበታል። በቀሪ ደቂቃዎች ግን ሌላ ሙከራ ሳይስተናገድ ጨዋታው ያለ ግብ ፍፃሜውን አግኝቷል።
ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ ነጥቡን 7 በማድረስ ሁለት ደረጃዎችን በማሻሻል 6ኛ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በስድስት ነጥቦች ተከታዩን ቦታ ይዟል።