ከፍተኛ ሊግ | ሻሸመኔ ከተማ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል

ኤፍሬም ዓለምነህን በዋና አሰልጣኝነት ሾሞ የነበረው ሻሸመኔ ከተማ አስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የነባሮችን ውልም አራዝሟል፡፡

በቅርቡ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት አገልግሎ የነበረው ኤፍሬም ዓለምነህን በዋና አሰልጣኝነት ምርጫው ያደረገው የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ ክለብ ሻሸመኔ ከተማ ለ2014 የውድድር ዘመን ተጠናክሮ ለመቅረብ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር በመፈፀም የነባር አስራ ሦስት ተጫዋቾችን ውልም ለተጨማሪ ዓመት አድሷል፡፡ ክለቡ ካስፈረማቸው አስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾች መካከል በርከት ያሉት ከአንደኛ ሊግ ክለቦች የመጡ ናቸው፡፡

ከዚህ ቀደም በሻሸመኔ ተጫውቶ ያሳለፈው እና በሲዳማ ቡና ፣ አዳማ ከተማ እና ባሳለፍነው አመት በሀላባ ከተማ ቆይታን ማድረግ የቻለው አጥቂው ፀጋዬ ባልቻን ጨምሮ ምንተስኖት ምትኩ (ግብ ጠባቂ ከቡሌ ሁራ) ፣ ጥላሁን ቦቶ ተከላካይ ከወላይታ ሶዶ) ፣ ምንተስኖት አበራ (አማካይ ከባቱ ከተማ) ፣ በሱፍቃድ ሞላ (ተከላካይ ከወላይታ ሶዶ) ፣ አምሳሉ መንገሻ (ተከላካይ ወልድያ ከተማ) ፣ ወጋየው ቡርቃ (ተከላካይ ከመድን) ፣ ቴዎድሮስ ታምሩ (አማካይ አርሲ ነገሌ) ፣ ኤቢሳ ከደር (ተከላካይ ከሆለታ) ፣ ምስጋና ሚኪያስ (አማካይ ከባሌ) ፣ ኑር አማን (አጥቂ ከሆለታ) እና ስጦታ ዋዳ (አማካይ ከቡሌ ሁራ) የክለቡ አዳዲስ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ከአዲሶቹ በተጨማሪ አስራ ሶስት ነባር ተጫዋቾችን ውል ያራዘመው ሻሸመኔ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከጀመረ ሰንበትበት ማለቱን ክለቡ ለድረገፃችን አሳውቋል፡፡