የሀዲያ ሆሳዕና እና አዳማ ከተማን ጨዋታን የመራው ዳኛ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎበታል

የሀዲያ ሆሳዕና እና አዳማ ከተማን ጨዋታን የመራው ዳኛ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎበታል

የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ከሰሞኑ ሲካሄድ ቆይቶ ከትላንት በስቲያ መገባደዱ ይታወሳል፡፡ ዕለተ ሰኞ ምሽት 1፡00 ላይ ከተካሄዱ ጨዋታዎች መካከል የሀዲያ ሆሳዕና እና አዳማ ከተማ ጨዋታ ተጠቃሹ ነው፡፡ ያለግብ የተጠናቀቀውን ይህንን ጨዋታ ፌዴራል ዋና ዳኛ ምስጋናው መላኩ እንደመራው የሚታወስ ሲሆን ዳኛውም ፈፀመ በተባለው የህግ ጥሰት የተነሳ ከቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መነሳቱ ታውቋል፡፡

43ኛው ደቂቃ ላይ የሀዲያ ሆሳዕና ተከላካዮች ለግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳ ኳስን ወደ ኃላ መልሰው ለማቀበል ሲጥሩ ኳሷ በማጠሯ የአዳማ ከተማው አጥቂ ዳዋ ሆቴሳ አልፎ ወደ ግብ ለማምራት በሚጥርበት ወቅት ግብ ጠባቂው ከሳጥን ውጪ ወጥቶ ኳሷን በእጁ በማስቀረቱ በረዳት ዳኛው ጠቋሚነት የቅጣት ምት ለአዳማ ከተማ ተሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የዕለቱ ዋና ዳኛ ምስጋናው መላኩ ግብ ጠባቂውን በማስጠንቀቂያ ካርድ ማለፋቸው መነጋገርያ የነበረ ሲሆን አዳማ ከተማዎችም ክስ አስይዘው እንደነበር የሚታወስ ነው።

ይህን ተከትሎ ዳኛው በፈፀመው የህግ ክፍተት መነሻነት በትናንትናው ዕለት በተላለፈ ውሳኔ በፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ላይ በዳኝነት እንዳይመራ መደረጉ ታውቋል፡፡

በተያያዘ ኮሚቴው በተደጋጋሚ የህግ ጥሰት እና ሌሎች ስህተቶችን የሚፈፅሙ ዳኞችን በየጊዜው እየጠራ የመገማገም ስራን እንደሚሰራ የተሰማ ሲሀን በዛሬው ዕለትም ጥቂት ዳኞችን ጠርቶ ምክክር እንደሚያደርግ ሰምተናል፡፡