ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በ4ኛ የጨዋታ ሳምንት ትኩረት የሳቡ የጨዋታ ሳምንቱ ዓበይት አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች የሦስተኛው ፅሁፋችን ተዳሰዋል።

👉 የቆሙ ኳሶችን መከላከል እና ማጥቃት

የእግርኳስን ውጤት በመሰረታዊነት የሚወስኑ አምስት ጉዳዮች እንደሆኑ ይታመናል። እነዚህ ኳስ በቁጥጥር ስር ስትሆን ፣ ከኳስ ውጭ ስትሆን ፣ ወደ መከላከል የሚደረግ ሽግግር ፣ ወደ ማጥቃት የሚደረጉ ሽግግሮች እና የቆሙ ኳሶች ናቸው።

የቆሙ ኳሶች (የማዕዘን ምት ፣ የቅጣት ምት እና የእጅ ውርወራ) ነጥለን ስንመለከት የቆሙ ኳሶችን መከላከል ፣ የቆሙ ኳሶችን ማጥቃት በሚል ከግለን መመልከት ይገባል።

በአሁኑ ወቅት ከቆሙ ኳሶች መነሻቸውን ያደረጉ ጎሎች ድርሻ በክለቦች እግርኳስ 30% የሚልቁ ሲሆን በዓለምአቀፍ የሀገራት ውድድር ደግሞ ይህን የቆሙ ኳሶች የግብ ድርሻ ከአጠቃላይ የግብ ምንጮች ጋር ሲነፃፃር ከ40% ይልቃል።

ታድያ ከአጠቃላይ ግቦች 30% – 40% የሚሆነው ከቆሙ ኳሶች የሚገኙ ከሆነ እውቁ ጀርመናዊ አሰልጣኝ እና በዘመናዊ እግርኳስ ታሪክ ደማቅ አሻራን በማሳረፍ ላይ የሚገኘው ራልፍ ራኚክ እንደሚለው የቡድኖች ልምምድ ቢያንስ በትንሹ 30% የሚሆነውን ጊዜያቸውን እነዚህን የቆሙ ኳሶች አጋጣሚዎች (Situation) የሚጠቁሙባቸውን መንገዶች ላይ ማተኮር አንዳለባቸው ያስረዳል፤ በሀገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ከዚህ በተፃራሪ የቆመ ነው።

ቡድኖች የቆሙ ኳሶችን የሚያጠቁበትም ሆነ የሚከላከሉበት መንገድ ፍፁም ያልተጠና እና እንዲያው በዘፈቀደ የሚደረጉ ስለመሆናቸው መናገር ይቻላል። በሰለጠኑት ሀገራት ቡድኖች በዚህ ረገድ ልቀው ለመገኘት የሙሉ ሰዓት የቆሙ ኳሶች አሰልጣኞችን በመቅጠር ጭምር በዚህ መንገድ በመላቅ ተጨማሪ ጥቂት ግቦችን ለማከል እየሰሩ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ በእኛ ሀገር አውድ ግን በልምምድ ሜዳዎች ላይ በዚህ ረገድ ሥራዎች በትኩረት ሲሰሩ አንመለከትም።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች በአጠቃላይ ከተቆጠሩ አስራ ሰባት ግቦች ውስጥ ስድስቱ (36%) የሚሆኑት የተቆጠሩት ከቆመ ኳስ መነሻነት መሆኑ ምናልባት የዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አስገራሚ እውነታ ነው።

የተቆጠሩትን ግቦች ለመመረመረ በመሰረታዊነት የሚያስተውላቸው እጅግ መሰረታዊ የሆኑ የቆሙ ኳስ የመከላከል ድክመቶች ናቸው። ደካማ የሆነ የሰው በሰው ወይንም በቀጠናዎች የመከላከል ድክመት በተጨማሪ ከቆመ ኳስ ለሚነሱ የመጀመሪያ ኳሶች ብቻ መዘጋጀት ይህም የሚያጠቃው ቡድን በሁለተኛ ኳሶች ተጠቃሚነቱ ሲጨምር ተመልክተናል። በተመሳሳይ ከኳሱ ቅርብ እና ሩቅ የሚገኙ ቋሚዎችን በሚዛናዊነት በመከላከል ረገድ ያለ ውዥንብር እንዲሁም ሌሎች ሀሳቦችን በመከላከሉ ረገድ ማንሳት እንችላለን።

ኳሶችን የሚያጠቁት ቡድኖች ግን በሙሉ በሚያስብል መልኩ በልምምድ ሜዳ ላይ የዳበሩ የማይመስሉ የአንድ ጊዜ ደመነፍሳዊ ሙከራዎች እንጂ የሚደጋገሙ ተመሳሳይ ነገሮች (Pattern) አለመልከታችን ቡድኖች የቆሙ ኳሶችን አጠቃቀማቸውን ለማሻሻል አሁንም ይበልጥ ጠንክረው መስራት እንደሚኖርባቸው ያስመለከተ አጋጣሚ ነበር።

👉 አስተርጓሚው ረዳት አሰልጣኝ

በድሬዳዋ ከተማ የአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ረዳቶች ከሆኑት አንዱ የሆነው ቶፊቅ እንድሪስ በዚህ የጨዋታ ሳምንት በአዲስ ሚና ብቅ ብለዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን 3-1 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በጨዋታው ሐት-ትሪክ የሰራው ማሊያዊው አጥቂ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከሱፐር ስፖርት ጋር በነበረው ቆይታ ወቅት ፈረንሳይኛን አቀላጥገው የሚናገሩት የድሬዳዋ ከተማው ምክትል አሰልጣኝ ቶፊቅ እንድሪስ ለማማዱ ሲዲቤ ጥያቄዎችን በመተርጎም እና ምላሾቹን ወደ አማርኛ በመመለስ ቃለ መይቁን ሲያሳልጡ ተመልክተናል።

👉 የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ተመልሰዋል

በመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት ቡድናቸው ከሰበታ ከተማ ጋር ያለ ግብ በአቻ ውጤት ሲለያይ ቡድናቸውን ከመሩ ወዲህ ከዕይታ ርቀው የሰነበቱት የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ዳግም በሜዳው ጠርዝ ተመልክተናቸዋል።

ወላጅ አባቴ አርፈዋል በሚል ምክንየት ወደ ሀገራቸው አቅንተው የነበሩት አሰልጣኙ በተመሳሳይ ምክንያት ከዚህ ቀደም ያሰለጥኑት ከነበረው ክለብ የመልቀቃቸው ጉዳይ እንዲሁ ከሀገራቸው ሆነ ለሌላ ኃላፊነት ከማመልከታቸው ጋር ተዳምሮ የአሰልጣኙ ቆይታ ላይ ብዙዎች ጥያቄ እንዲያነሱ ያስገደደ ነበር።

የሆነው ሆኖ አሰልጣኙ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ቡድናቸው ከመከላከያ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ቡድናቸው በሜዳ ተገኝተው መርተዋል።

👉 ለሊጉ ሌላ ቅመም እየጨመሩ የሚገኙት መሳይ ተፈሪ

በሜዳ ላይ የሚታዩ የጨዋታ ሀሳቦች እጥረት ክፉኛ በታመመው ሊጋችን እንደ መሳይ ተፈሪ ያሉ የራሳቸው የሆነ የጨዋታ መንገድ ቡድኖቻቸው ላይ ለማስረፅ የሚሞክሩ እና ይህንን ሜዳ ላይ ለማሳየት የሚታትሩ አሰልጣኞች ቁጥር ቀስ በቀስ እየጨመረ መምጣት ሊጉን የተለየ ጣዕም እየሰጠው ይገኛል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሊጉ ጨዋታዎች ይህ ነው የሚባል የጨዋታ ዕቅድ ለማየት የምንቸገርባቸው ምናልባት አገላገፁ ተገቢ ባይሆንም በዘፈቀደ በሚጫወቱ ሁለት ቡድኖች መካከል የሚደረጉ የሚመስሉ ጨዋታዎች በሊጉ በርካታ ነበሩ። አሁን ላይ በተወሰነ መልኩ የሚያደርጉትን የሚያውቁ ምክንያታዊ አሰልጣኞች በሊጉ ብቅ ማለት ጀምረዋል።

ከእነዚህም መካከል ከጥቂት ዓመታት በፊት ወላይታ ድቻን ወደ ፕሪሚየር ሊግ በማሳደግ በሊጉ በተለየ የጨዋታ መንገድ ተፎካካሪ ቡድን መገንባት የቻሉት መሳይ ተፈሪ ለመጨረሻ ጊዜ በፋሲል ከነማ ከነበታቸው ቆይታ በኋላ ለጥቂት ዓመታት ከፕሪሚየር ሊጉ ርቀው የቆዩ ቢሆንም አሁን ላይ ዳግም በፕሪሚየር ሊጉ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ብቅ ብሏል።

አንደኛው አብዛኛዎቹ የሊጉ አሰልጣኞች የሚወቀሱበት ጉዳይ ቡድናቸው እንዲጫወት የሚፈልጉበትን መንገድ ወደ ተጫዋቾቻቸው በማስረፅ ሀሳባቸውን በሜዳ ላይ ወደሚታይ እውነታ (Reality) የመቀየር ችግር ነበር። ለአብነትም በጥብቅ መከላከል ቡድኑ እንዲጫወት የሚልገው አሰልጣኝ ቡድኑ መከላከሉን በወጉ ለመከወን ሲቸገር በተመሳይይ ኳስን መቆጣጠር የሚፈልግ ቡድን መገንባት እንሻለን የሚሉ አሰልጣኞች ደግሞ ቡድናቸው ይህን ለማድረግ ሲቸገር ብሎም ቡድኖች መሰረታዊዎችን ፅንሰ ሀሳቦች በወጉ መተግበር ሲሳናቸው እንመለከታለን።

የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድኖች ግን የራሳቸው መገለጫ ያላቸው እንዲሁ በጨዋታ ዕቅዳቸው የነደፉትን ሀሳብ በወጉ ሜዳ ላይ የሚከውኑ ሆነው እያስተዋልን እንገኛለን። መከላከል ሲፈልግ ቡድኑ በደንብ ጠቅጠቅ ብሎ የሚከላከል እንደዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በላይኛው የሜዳ ክፍል ጫና አሳድሮ መጫወት ሲሻ ይህን በአመርቂ መልኩ ሲተገብሩ ተመልክተናል።

መሰል ሀሳብ ያላቸው አሰልጣኞች በሊጉ እየበዙ መሄዳቸው የሊጉን የእግርኳሳዊ ፉክክር ደረጃ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ፀጋዬ ኪዳነማርያም ወደ ሀዲዱ ይመለሱ ይሆን?

በአሁኑ ወቅት በወላይታ ድቻ አሰልጣኝነት መንበር ላይ የሚገኙት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በተወሰነ መልኩ ተንገራግጮ የነበረውን የአሰልጣኝነት ጉዟቸውን ዳግም ወደ መስመር ለመመለስ በወላይታ ድቻ ቤት ጥሩ ሥራን እየሰሩ ይገኛል።

በአሰልጣኝነት ህይወታቸው ጅማሮ በትራንስ ኢትዮጵያ እና ሐረር ቢራ ጠንካራ ቡድኖች በመገንባት የሚታወቁት ፀጋዬ ኪዳነማርያም ከዚያ በኋላ በያዟቸው ክለቦች የነበረው ቆይታ እምብዛም በአውንታዊነት የሚነሱ አልነበሩም። አምናም በጅማ አባ ጅፋር እርግጥ ቡድኑ በመደበኛው ውድድር በሊጉ የሚያቆየውን ውጤት ማግኘት ባይችሉም ከፍተኛ መሻሻሎችን ያሳየ ቡድንን ግን በሁለተኛው ዙር አሳይተውን ነበር።

ዘንድሮም በወላይታ ድቻ ቤት ከሌሎች ክለቦች አንፃር በአነስተኛ የዝውውር በጀት ጥቂት ተጫዋቾችን አዘዋውረው ያለ በቂ የወዳጅነት ጨዋታ ወደ ውድድር ቢገቡም በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረችባቸው ግብ ሽንፈት ካስተናገዱ ማግስት በተከታታይ ያደረጓቸውን ሦስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ወደ ሰንጠረዡ አናት መምጣት ችለዋል።

እርግጥ ውድድሩ ገና ረጅም ቢሆንም አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በወላይታ ድቻ እየሰሩት የሚገኙት ነገር የአሰልጣኝነት ጉዟቸውን ዳግም ወደ መስመር ሊመልስ እንደሚችል ፍንጮች እያሳዩ ይገኛል።