የመጨረሻው ፅሁፋችን ትኩረት የሚሹ ሌሎች ጉዳዮች ቀርበውበታል።
👉 “ጎፈሬያማ” ፕሪምየር ሊግ
ከ2013 የውድድር ዘመን አንስቶ “ጎፈሬ” የተሰኘው ሀገር በቀል የትጥቅ አቅራቢ ኩባንያ ቀስ በቀስ የገበያ ድርሻውን እያሳደገ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ከፕሪሚየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ጋር ይፋዊ ስምምነቶችን እየፈፀመ ይገኛል።
ለሲዳማ ቡና የተለያዩ የመጫወቻ እና የልምምድ መለያዎችን በማቅረብ ትውውቁን ያደረገው ኩባንያው የዝግጅት ጊዜ ውድድርን በማዘጋጀት ቀጥሎ አሁን ላይ በቁጥር ስምንት ከሚጠጉ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ጋር ይፋዊ እና ይፋ ባልተደረገ መልኩ የትጥቅ አቅርቦት ስምምነቶችን በመፈፀም አድማሱን እያሰፋ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በዘፈቀደ ለክለቡ ይፋዊ ቀለም አማራጮች የቀረቡ የቀለም ስብጥር ያላቸው በቀላሉ ገበያ ላይ የሚገኙ መለያዎችን የክለቦች ይፋዊ መለያ አድርጎ የመጠቀም ባስ ሲል ደግሞ በአማራጭ መለያነት ቡድኖች የሚጠቀሙባቸው መለያዎቹ የአብዛኛዎቹ ተመሳሳይ የነበረበት ጊዜ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ይህን ቸልተኝነት የታከለበትን የገነገነ ኋላ ቀር እሳቤ እንደ ጎፈሬ ያሉ ይፋዊ ትጥቅ አቅራቢዎች መምጣታቸው ይህን አስተሳሰብ ለመስበር ረገድ ዓይነተኛ ሚናን ይወጣል።
መሰል ስምምነቶች ከወጪ ቅነሳ አንፃር ለክለቦቹ ከሚሰጡት ጠቀሜታ ባሻገር በክለቦቻችን ብዙም ቦታ በማይሰጠው የክለባዊ ማንነት ግንባታ ላይ ጉልህ ሚናን መወጣት በሚችሉ የክለቦቹ ብቻ የሆኑ እና የክለቦቹ መገኛ አካባቢዎችን የሚወክሉ የተለየ የመለያ ንድፎች ጥቅም ላይ መዋል መጀመራቸው ራሱ አበረታች ልምምድ ነው።
ኩባንያው አሁን በያዘው አካሄድ የሚቀጥል ከሆነ በሀገራችን እግርኳስ የትጥቅ አቅርቦት ረገድ ቀዳሚው ሀገር በቀል ተቋም የመሆኑ ጉዳይ የሚቀር አይደለም።
👉 ተቀፅላ ስሞች በመለያ ላይ
ሊጋችን የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ማግኘቱን ተከትሎ በቀደመው ጊዜ እንደ ብርቅ ይታይ የነበረው የተጫዋቾች ስም በመለያዎች በስተጀርባ የመመልከታችን ጉዳይ አሁን ላይ እየተለመደ መጥቷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በመለያዎች በስተጀርባ በሚሰፍሩ ስያሜዎች ጋር ከዚህ ቀደም በሆሄያት ግድፈት ዙርያ ሀሳቦችን ማንሳታችን አይዘነጋም። አሁን ደግሞ የተጫዋቾች ተቀፅላ ስሞች በክለብ መለያዎች ላይ ሰፍረው መመልከት ጀምረናል። ለአብነትም የድሬዳዋ ከተማው ግብጠባቂ ፍሬው ጌታሁን በመለያው ላይ “ፍሬ” በሚል ሲገለፅ በተመሳሳይ የሀዋሳ ከተማው አማካይ ወንድማገኝ ኃይሉ ደግሞ “ፎቼ” በሚል አካባቢያዊው መጠርያ መለያ ላይ ታትሞ ተመልክተናል።
👉 የሊጉ ዳግም መመለስ
በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ምክንያት ለ18 ያህል ቀናት ተቋርጦ የነበረው ፕሪሚየር ሊጉ ከዕረፍት ሲመለስ የተለያዩ ያልተጠበቁ ነገሮች ተከስተውበታል።
ብዙ ሲተች የነበረው የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ የተወሰኑ ማሻሻያዎች ይደረጉበታል ተብሎ ቢጠበቅም ሜዳው መጠነኛ ዕረፍት ከማግኘቱ ጋር በተያያዘ የመጫወቻ ሳሩ በመጠኑም ቢሆን አረንጓዴያማ መልኩን መልሶ ከማግኘቱ ባለፈ ይህ ነው የሚባል መሻሻሎች ሳንመለከትበት ዳግም ሊጉ ጅማሮውን አድርጓል።
ሊጉ እስኪቋረጥ ድረስ በተሻለ የማሸነፍ ግስጋሴ ላይ የነበሩት ፋሲል ከነማ እና ባህርዳር ከተማ የሊጉ መቋረጥ የነበራቸውን የማሸነፍ ግስጋሴ እንዳያስቀጥሉ እክል የሆነባቸው ይመስላል። ሁለቱም ቡድኖች ከዕረፍት መልስ ባደረጓቸው የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታዎች በተጋጣሚዎቻቸው አንፃራዊ የበላይነት ተወስዶባቸው በተመሳሳይ 2-1 በሆነ ውጤት የተሸነፉ ሲሆን ወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከተማ በሰፊ የግብ ልዩነት ያሸነፉ ቡድኖች ናቸው።
ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ያለ ግብ በተጠናቀቁበት የጨዋታ ሳምንቱ በድምሩ አስራ ሰባት ግቦች የተቆጠሩበትም ነበር።
👉 አምና የወጣው ህግ ዘንድሮ መተግበር ጀምሯል
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሼር ካምፓኒ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት መጀመሪያ ላይ ካወጣቸው ህጎች መካከል በዕረፍት ሰዓት በቋሚ አሰላለፍ የነበሩ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል ሲገቡ በተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበሩ ሁሉም ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል መግባት አለባቸው የሚለው አንዱ ነበር።
ይህንን ህግ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለዳኞች ኃላፊነት የተሰጠ ሲሆን ባለፈው ዓመት ይህን ህግ ተፈፃሚ ሳያደርጉ የቆዩ ቢሆንም ዘንድሮ ህጉ ሥራ ላይ ውሏል። በዚህም ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች በተለመደው መልኩ ተጠባባቂዎች በዕረፍት ጊዜ ሜዳ ላይ መሀል ባልገባ እየተጫወቱ ወይንም ሰውነታቸውን ሲያፍታቱ ከመቆየት ይልቅ ወደ መልበሻ ክፍል በመግባት ከቀሪው ስብስብ ጋር የዕረፍት ጊዜ ምክክሩ ተካፋይ ሆነዋል።
👉 የዳኞች መገናኛ መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋል
በውጪ ሀገራት የእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይ ዳኞች በጆሯቸው ላይ የመነጋገራያ መሳሪያ ሰክተው እርስ በእርሳቸው በቀላሉ መረጃዎችን ሲለዋወጡ እና በሜዳ ላይ የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች ሲያሳልጡ ይስተዋላል። በሀገራችን ሊግ የዳኝነት አካሄድ ላይ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲነሳ ቢስተዋልም ሥራውን በቴክኖሎጂ የማገዝ ጉዳይ ላይ ግን እንደሀገር በቂ ጥረት ሲደረግ አይታይም። ሆኖም ለአብነት ይህንን የመነጋገራያ መሳሪያ ውስን ዳኞች በግላቸው በመግዛት በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ሲጠቀሙ ይታይ ነበር። በዚህ ሳምንት ግን አብዛኞቹ ጨዋታዎች ላይ ቴክኖሎጂው ተተግብሮ መመልከታችን ትኩረታችንን ስቦታል። ጉዳዩ ላይ እንደ ሀገር የተሰራ ሥራን ተከትሎ የታየ ለውጥ እንደሆነ ለማጣራት ባደረግነው ጥረት ግን አሁንም ከግለሰቦች ጋር የተያያዘ ሆኖ አግኝተነዋል።
መነጋገሪያ መሳሪው በዚህ ሳምንት ካዳኙ ዳኞች ውስጥ ኢንተርናሽናል ዳኞቹ ቴዎድሮስ ምትኩ እና በላይ ታደሰ ያላቸው ከመሆኑ ባሻገር አዳነ ወርቁ እና እያሱ ፈንቴም በግላቸው እንዳገኙት ማወቅ ችለናል። በዚህ ሳምንት ከአንድ ጨዋታ ውጪ ሌሎቹ ላይ ጥቅም ላይ ውሎ የተመለከትነውም እርስ በእርስ በመዋዋስ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።