የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ሙሉ ሽፋን የምትሰጠው ሶከር ኢትዮጵያ ከትናንት በስትያ የተጠናቀቀው የአራተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ምርጥ ቡድን በሚከተለው መልኩ መርጣለች።
አሰላለፍ፡ 3-4-3
ግብ ጠባቂ
ሲልቪያን ግቦሆ (ወልቂጤ ከተማ)
ግዙፉ የግብ ዘብ ሲልቪያን ቡድኑ ወልቂጤ ሀዋሳ ከተማ ላይ የዓመቱን የመጀመሪያ ድል ሲያገኝ የነበረው ሚና የላቀ ነበር። ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን ሲያመክን የነበረው ተጫዋቹ የኋላ መስመሩን የተረጋጋ እንዲሆን ካሳየው የመምራት ብቃት በተጨማሪ ቡድኑ ግብ ካስቆጠረ በኋላ የነበረበትን ጫና በሚገባ መመከት መቻሉ በቦታው ተመራጭ አድርጎታል።
ተከላካዮች
ልመነህ ታደሠ (አዲስ አበባ ከተማ)
በሳምንቱ ከተመዘገቡ አስገራሚ ውጤቶች መካከል አዲስ አበባ ከተማ ፋሲል ከነማን የረታበት ይጠቀሳል። በጨዋታው ቡድኑ ከነበረው አስገራሚ የመጀመሪያ አጋማሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ በተጨማሪ ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ የነበረው የመከላከል እንቅስቃሴ ድንቅ ነበር። በተለይ ፋሲል ወደ ጨዋታው ለመመለስ በሚታትርበት ጊዜ ሳይረበሽ የአየር እና የመሬት ላይ የአንድ ለአንድ ፍልሚያዎችን ሲያሸንፍ የነበረው የመሐል ተከላካዩ ልመነህ ታደሰ ከኋላ በምናዋቅረው የሦስትዮች የተከላካይ መስመር ላይ ቦታ አግኝቷል።
አሌክስ ተሰማ (መከላከያ)
ከዚህ ቀደም በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ቦታ አግኝቶ የነበረው አሌክስ ተሰማ ባሳለፍነው ሳምንት ያሳየውም ብቃት ድጋሜ ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ እንዲካተተ አድርጎታል። እርጋታ የተሞላበት እንቅስቃሴ ሲያደርግ የሚስተዋለው አሌክስ ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ሲጋራ የነበረው የቦታ አጠባበቅ፣ ኳስ የማፅዳት እና የረጃጅም ኳሶች ስኬት ጭብጨባ የሚያስቸረው ነበር። በተለይ ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ በጊዮርጊስ በኩል የነበረውን ጫና በስኬታማ ሸርተቴዎቹ እና ኳስ የማፅዳት ብቃቱ ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓል።
ሳሙኤል አስፈሪ (አዲስ አበባ ከተማ)
ከልመነህ ታደሠ ጋር በመሆን ጥሩ የጨዋታ ሳምንት ያሳለፈው ተጨዋች ሳሙኤል አስፈሪ ነው። ተጫዋቹ የነበረው ቀልጣፋ እንቅስቃሴ የፋሲል ከነማ ከወገብ በላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ከእንቅስቃሴ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል። ከአጣማሪው ልመነህ ጋር የነበረው መናበብም ጥሩ ነበር። በጨዋታውም በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የመሐል ተከላካይ ሆኖ በተጫወተበት ጨዋታ (በሁለተኛ ሳምንት በነበረው ጨዋታ የመስመር ተከላካይ ሆኖ መጫወቱ ልብ ይሏል) ያሳየው ብቃትም በቦታው ተመራጭ ሆኖ እንዲዘልቅ የሚያደርገው ይመስላል።
አማካዮች
እንየው ካሣሁን (ድሬዳዋ ከተማ)
በቀኝ ተመላላሽ ቦታ የተጠቀምነው ተጫዋች የድሬዳዋ ከተማው አይደክሜ እንየው ካሳሁን ነው። ድሬዳዋ ጅማን ሦስት ለአንድ ሲረታ የመጀመሪያውን የሲዲቤ ጎል አመቻችቶ ያቀበለው ተጫዋቹ በእንቅስቃሴዎችም የነበረው አጠቃላይ የማጥቃት እና የመከላከል ብርታት ጥሩ ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ ቡድኑ የሜዳውን የጎንዮሽ ስፋት ተጠቅሞ የተጋጣሚ ተከላካዮች እንዲዘረዘሩ የተጫዋቹ ሚና ከፍተኛ ነበር። ከዚህ ውጪ ደግሞ ለስኬታማነት የተጠጉት ተሻጋሪ ኳሶቹ ለጅማዎች ፈተና ሲሆን ተስተውሏል።
ኢማኑኤል ላሪያ (መከላከያ)
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በስድስት ቁጥር ሚና የነጠረ ብቃት ያሳየ ተጫዋች ባይኖርም በአንፃራዊነት ለተከላካዮች ተገቢ ሽፋን ሲሰጥ የነበረው የመከላከያው ጋናዊው አማካይ ኢማኑኤል ላሪያ ነው። በአራቱም የሊጉ ጨዋታዎች በአንፃራዊ ወጥ ብቃት ሲጫወት የነበረው ላርያ የቅዱስ ጊዮርጊስ ማጥቃት መሐል ለመሐል እንዳይሆን በማድረጉ ረገድ ተሳክቶለት ነበር። በተጨማሪም በመጀመሪያው አጋማሽ ከእግሩ ሲነሱ የነበሩት ረጃጅም ኳሶች አደጋን ለመፈፀም የተቃረቡ ነበር።
ኤሊያስ አህመድ (አዲስ አበባ ከተማ)
ሌላኛው ስኬታማ የጨዋታ ሳምንት ያሳለፈው ተጫዋች የአዲስ አበባ ከተማው አማካይ ኤሊያስ አህመድ ነው። የመዲናው ክለብ አዲስ አበባ የወቅቱን የሊጉን ሻምፒዮን ፋሲል ሲረታ የማሸነፊያው ጎል የተቆጠረው በኤሊያስ ነበር። ከኳስ ጋር የሚያሳልፈው ጊዜ የተዋጣለት ኤሊያስ ኳስ እና መረብን በ39ኛው ደቂቃ ከማወዳጀቱ በተጨማሪ የአማካይ እና የአጥቂ መስመሩን በማገናኘት ረገድ የተዋጣለት ነበር። በተለይ ፈጣን እንቅስቃሴው ለፋሲል የወገብ በታች ተጫዋቾች የራስ ምታት ነበር።
ሀቢብ ከማል (አርባምንጭ ከተማ)
በአራተኛ የጨዋታ ሳምንት ጎልቶ የወጣው ስም ሀቢብ ከማል ነበር። የአርባምንጩ የመስመር ተጫዋች በባህር ዳሩ ጨዋታ ካስቆጠራት ድንቅ የቅጣት ምት ጎል በተጨማሪ ሌሎች ግቦችንም ለማግኘት የነበረው የግል ተነሳሽነት እጅግ ከፍተኛ ነበር። በወረቀት ላይ ከመስመር እየተነሳ እንዲያጠቃ ሀላፊነት ተሰጥቶት የነበረው ሀቢብ ወደ መሐል ሰብሮ በመግባትም በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን ከርቀት ሲፈጥር ነበር። ተቀይሮ እስከወጣበት 79ኛው ደቂቃ ድረስም በከፍተኛ ታታሪነት ቡድኑ እንዳይጠቃ ወደ ኋላ እየተመለሰም ድጋፍ ሲሰጥ ነበር።
አጥቂዎች
ሪችሞንድ አዶንጎ (አዲስ አበባ ከተማ)
ድንቅ ከነበረው የአዲስ አበባ ቡድን የተካተተው ሌላኛው ተጫዋች ሪችሞንድ አዶንጎ ነው። ዓምና በድሬዳዋ ከተማ እስከ 23ኛው የጨዋታ ሳምንት ድረስ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ተስኖት የነበረው ሪችሞንድ በከባዱ የፋሲል ጨዋታ በሁለት ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል። አንድ በማስቆጠር አንድ በማቀበል። እርግጥ አጋጣሚዎችን የመጠም ክፍተት አሁንም ቢታይበትም በመጨረሻው ጨዋታ የነበረው ብቃት ሻል ያለ ነበር። ከዚህ ውጪ ደግሞ በጥሩ ታታሪነት ቡድኑ ጥቃቶች በበረከቱበት ሰዓት ወደ ኋላ እየተመለሰ እገዛ ሲሰጥ ነበር።
ስንታየሁ መንግሥቱ (ወላይታ ድቻ)
ባሳለፍነው ሳምንት በብቸኝነት የሳጥን ውስጥ አጥቂ በመሆን መጫወት የሚችሉ ሦስት ተጫዋቾች ጥሩ ቀን አሳልፈዋል። አንዱ ደግሞ የወላይታ ድቻው ቁመታም አጥቂ ስንታየሁ መንግስቱ ነው። እርግጥ ተጫዋቹ ኳስ እና መረብን እስኪያገናኝ ድረስም ሆነ ካገናኘ በኋላ ሌሎች አጋጣሚዎችን ሲያመክን ቢታይም በወሳኝ ሰዓቶች አይምሬነቱን ያሳየበትን ጎሎች በ49ኛው እና 66ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል። በተለይ የቡድኑ አሠልጣኝ በጨዋታው ለነበራቸው ቀጥተኛ አጨዋወት የተመቸ ሆኖም ቀኑን በጥሩ ብቃት አሳልፏል።
ማማዱ ሲዲቤ (ድሬዳዋ ከተማ)
በሳምንቱ ብቸኛው ባለ ሐት-ሪክ ተጫዋች የሆነው ማማዱ ሲዲቤ ምርጥ የጨዋታ ቀን በግልም እንደ ቡድንም አሳክቷል። ተጫዋቹ በወሳኝ እንቅስቃሴዎች ላይ የነበረው የቦታ አያያዝ ችሎታም የተሟላ ሐት-ሪክ (በግንባር፣ በግራ እና በቀኝ እግር የተቆጠሩ) እንዲሰራ አድርጎታል። ይህ የአጥቂ ባህሪን መላበሱም በሚገባ ታይቶ ቡድኑ ተጠቅሞ ወጥቷል። ከዚህ ውጪ ጀርባውን ለጎል እየሰጠ ከአጋሮቹ ጋር እየተናበበ የሚጫወትበት መንገድም የተሻለ ነበር።
አሠልጣኝ
ደምሰው ፍቃዱ (አዲስ አበባ ከተማ)
በጊዜያዊ አሠልጣኝነት ቦታ መንበረ ስልጣን የተሰጣቸው ደምሰው ፍቃዱ ቡድናቸው ሁለተኛ ተከታታይ ድል አግኝቷል። ከምንም በላይ ደግሞ በአራተኛው ሳምንት የወቅቱን የሊጉን አሸናፊ እና የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማን ያሸነፈው ቡድናቸው በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ያሳየው ብቃት ግርምትን የሚጭር ነበር። በስብስብ እና በተጫዋቾች ጥራት ረገድ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለ የሚመስለውን ልዩነት በፍላጎት ብቻ ፍርሽ ያደረጉበት መንገድም የሚደነቅ ነው። ተጫዋቾቹ በታታሪነት እንዲጫወቱ ያስቻሉበት እና የፋሲልን ጠንካራ የማጥቃት ሀይል የተቆጣጠሩበት እንዲሁም እምብዛም የማይደፈረውን የኋላ መስመር ያፍረከረኩበት መላ የሳምንቱ ምርጥ አሠልጣኝ ቦታን ያለ ከልካይ እንዲያገኙት አድርጓል።
ተጠባባቂዎች
ክሌመንት ቦዬ
ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ
ሄኖክ ኢሳይያስ
መሐመድ አብዱለጢፍ
አብዱልከሪም ወርቁ
በረከት ወልዴ
ፍፁም ጥላሁን