ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የአምስተኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታን የተመለከቱ ጉዳዮችን እንዲህ አንስተናል።

ይህንን ጨዋታ ስናስብ የሀዲያ ሆሳዕና የአምናው የደመወዝ ውዝግብ ፈንድቶ የወጣበት እና ባልተሟሉ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ የገባው በሁለተኛው ዙር ከሀዋሳ ከተማ ጋር ሲገናኝ የነበረ መሆኑን ያስታውሰናል። በወቅቱ የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ የነበሩት ሙሉጌታ ምህረት አሁን በሀዲያ በኩል የምናያቸው መሆኑ ደግሞ ሌላው ግጥምጥሞሽ ነው።

በእስካሁኑ ውድድር ሀዋሳ በተሻለ ደረጃ ላይ ይቀመጥ እንጂ የሁለቱም አጀማመር የተዋጣለት የሚባል አይደለም። ሀዋሳ ከተማ ሁለት ድል እና ሁለት ሽንፈት ከማስመዝገቡ ባሻገር በሲዳማው ድል የነበረውን ጥንካሬ በወልቂጤው ጨዋታ መድገም አለመቻሉ ያልተጠበቀ ሆኖ አልፏል። ሁለት ነጥቦችን የያዘው ሀዲያ ሆሳዕናም እስካሁን የድልን መንገድ ማግኘት አልቻለም።

ሀዋሳ ከተማ ሲዳማን ሲረታ በነበረው የቡድን መዋቅር ከአጠቃላይ ስብስቡ ታታሪነት እና ክፍተት ያለመስጠት ትኩረት ውስጥ አጥቂዎቹ በተለይም የመስመር አጥቂዎቹ ሚና ጎልቶ ታይቶ ነበር። በማጥቃቱም በኩል እንዲሁ ዋና የቡድኑ መሳሪያ ይሆኑት የዚሁ ቦታ ተሰላፊዎች ተፅዕኖ ከፍታ ግን የራሱን አሉታዊ ጎን ይዞ የመጣ ይመስላል። ተጫዋቾቹ ጥሩ ቀን ባላሳለፉበት የወልቂጤው ጨዋታ ቡድኑም በአቅም ወርዶ መታየቱ ለተገማችነት እንዳያጋልጠው ስጋትን ይጭራል።

በዚህ ላይ የነገ ተጋጣሚው በቀድሞው አሰልጣኙ የሚመራ በመሆኑ እና አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በርከት ካሉት ተጫዋቾች ጋር አብረው መስራታቸው ተገማችነቱን ከፍ ሊያሰርገው ይችላል። በመሆኑም በተለይም በማጥቃት አማራጮቹ ላይ የአጥቂ አማካዮቹም ሚና የሚያጎላ የተለየ የጨዋታ ዕቅድ ይዞ ወደ ሜዳ በመግባት ለተጋጣሚ ግብረ መልስ የመስጠት አቅሙ ከወትሮው ከፍ እንዲል ያስፈልገዋል።

በሀዲያ ሆሳዕና በኩል የዲስፒሊን ጉዳይ ትኩረትን ይስባል። ቡድኑ በሦስት ሳምንታት ውስጥ ሦስት ተጫዋቾችን በቀይ ካርድ ማጣቱን ስንመለከት በሙሉ ስብስቡ ጨዋታዎችን አለመጨረሱ የጎዳው ይመስላል። መሰል ሁኔታዎች ከቀጠሉ ደግሞ እንደነገው ዓይነት ወሳኝ ነጥብ የሚያስፈልግባቸው ጨዋታዎች ላይ የጨዋታ ዕቅድ መፋለስ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ።

ከዚህ ባለፈ ቡድኑ አሁንም የአጨራረስ ችግሩ አለመቀረፉ ትልቁ ችግሩ ሆኖ ቀጥሏል። ችግሩን በተጫዋቾች አደራደር ለውጥ ለመፍታት የተሞከረበት የአዳማው ጨዋታም የተፈለገውን ውጤት አላስገኘም። በነገው ጨዋታ ደግሞ ከጉዳት ጋር የያይዞ አዲስ የፊት መስመር ጥምረት እንደምናይ ይጠበቃል። ከዕረፍቱ መልስ በተደረገው የሦስተኛው ሳምንት ጨዋታ ግን የተሻለ ሆኖ ይታይ የነበረው የቡድኑ ወደ ግብ የመድረስ አቅምም ጥያቄ እንዲነሳበት የሚያደርግ ነበር። ከስብስቡ አዲስነት አንፃር አሁን ላይ በቂ ውህደት ባይጠበቅም ቢያንስ ቡድኑ በሙሉ በራስ መተማመን ጨዋታዎችን እንዲከውን የመጀመሪያውን ድል ከቀናው ትልቅ ስኬት ይሆንለታል።

በጨዋታው ሀዋሳ ከተማ አብዱልባስጥ ከማልን በቅጣት ከማጣቱ በቀር የጉዳት ዜና የለበትም። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ሄኖክ አርፌጮ ከጉዳት ያልተመለሰ ሲሆን ባዬ ገዛኸኝ እና መሳይ አያኖም በተመሳሳይ ጨዋታው ያልፋቸዋል። በሌላ በኩል ኤፍሬም ዘካሪያስ ቅጣት ላይ ሲሆን ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ግን ቅጣቱን ጨርሶ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል።

ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ አዳነ ወርቁ በመሀል ዳኝነት ለመምራት ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ በሊጉ እስካሁን በአራት አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ሁለቱን በአቻ ውጤት አጠናቀው ሁለቱን ሀዋሳ ከተማ ማሸነፍ ችሏል። በጨዋታዎቹ 11 ጎሎች ሲቆጠሩ ሀዋሳ ከተማ ዘጠኙን ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ አምስቱን ከመረብ አገናኝተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

ብርሃኑ በቀለ – ፍሬዘር ካሳ – ኤሊያስ አታሮ – እያሱ ታምሩ

ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን

ዑመድ ዑኩሪ – ሀብታሙ ታደሰ – ፀጋዬ ብርሃኑ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

መሐመድ ሙንታሪ

ዳንኤል ደርቤ – ላውረንስ ላርቴ – ፀጋሰው ድማሙ – ዮሃንስ ሱጌቦ

ወንድማገኝ ኃይሉ – ዳዊት ታደሰ – በቃሉ ገነነ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ