የነገ ምሽቱን ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተነዋል።
ሦስተኛው የጨዋታ ሳምንት እነዚህን ተጋጣሚዎች ባልተጠበቀ የውጤት መንገድ ውስጥ ያሳለፈ ነበር። በመቶ ፐርሰንት አሸናፊነት የዘለቀው ፋሲል ከነማ ባልተጠበቀ መልኩ በአዲስ አበባ ከተማ የተረታበት መንገድ ግምቶችን ያፋለሰ ሆኗል። በተቃራኒው ደግሞ አርባምንጭ ከተማ ለአሸናፊነት ተገማች ባልነበረበት የባህር ዳሩ ጨዋታ ድልን ማጣጣም መቻሉ አስደናቂ ነበር። ይህ ሁኔታም የነገውን ጨዋታ ውጤት መገመት ቀላል እንዳይሆን ያደረገ ነው ማለት ይቻላል።
ለፋሲል ከነማ የአዲስ አበባው ሽንፈት እንደ ማንቂያ ደውል የሚወሰድ ነው። ትኩረት በተዛነፈበት ሁኔታ ውስጥ የትኛውም ቡድን ከግስጋሴው የመግታት አቅም እንዳለው ትምህርት የወሰደበት በመሆኑ በነገው ጨዋታ በተለመደው ተነሳሽነት ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል። እምብዛም በቡድኑ ውስጥ የማይታዩ ግለሰባዊ እና የአደረጃጀት ችግሮች ግቦችን እንዲያስተናግድ ምክንያት ስለሆኑትም በዚህ ረገድ በመሻሻል በቶሎ ማገገም የቡድኑ ዋና የነገ ትኩረት ነው።
ጨዋታው ለአርባ ምንጭም ሌላ መልክ ይዞ የሚመጣ ነው። ዳግም ወደ ሊጉ ከተመለሰ በኋላ ተገማች ሳይሆን ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦች የሰበሰበው አርባምንጭ አሁን ላይ ቀላል ተፎካካሪ አለመሆኑን አሳይቷል። ይህ ደግሞ እንደ ነገ ተጋጣሚው ያሉ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች ከታች እንዳደገ ሳይሆን እንደቅርብ ተፎካካሪ አስበውት ወደ ሜዳ መግባታቸው አይቀርም። ቡድኑ ራሱን ትከሻ ለትከሻ በሙያፎካክሩ ጨዋታዎች ላይ ብልጫ ወስዶ የሚወጣበትን ፈተናም ከነገ የሚጀምር ይመስላል።
ከአጨዋወት አንፃር ስንመለከተው ፋሲል ከኳስ ጋር አርባምንጭ ደግሞ ያለኳስ የሚሆኑባቸው ቅፅበቶች አጓጊ ፍልሚያዎችን እንደሚያስመለክቱን ይጠበቃል። ፋሲል በአዲስ አበባው ጨዋታ የታየበት መቻኮል እና ኳሶችን የማባከን ድክመት ተቀርፎ ከመጣ በሌሌቹ ጨዋታዎች ወደ መሀል ሜዳ በተጠጋ የኋላ ክፍል ኳስ መስርቶ ለመውጣት የሚያደርገው ጥረትን እንደሚተገብር ይጠበቃል። ይህ ሁኔታ ደቂቃዎች ሲሄዱ ፋሲል ገፍቶ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በመግባት በተለይ ከመስመር ዕድሎችን እንዲፈጥር ሲያስችለው ታይቷል። ሆኖም ይህ ዕቅድ በራሳቸው ሜዳ ላይ መቆየትን ከሚመርጡ ተጋጣሚዌች ጋር ነበር የተመለከትነው።
የአርባምንጭ ከተማ የባህር ዳሩ ጨዋታ አካሄድ ግን ከዚህ የተለየ ነው ተጋጣሚን ወደራሳቸው ሜዳ ሳይገባ ጫና በመፍጠር ፍሰቱን በማቋረጥ በቶሎ ወደ ግብ የመድረስ ጀብደኝነትን የቀላቀለ አቀራረባቸው ውጤት አስገኝቶላቸዋል። ይህን አካሄድ ነገም ከደገሙት ከተሰላፊዎቹ ከፍተኛ ተነሳሽነት ጋር ተዳምሮ የቡድኑን ድንገተኛ ጥቃቶች ስል ሊያደርጋቸው ይችላል። ለዚህ ሁኔታ የሚኖረው የፋሲሎች ምላሽ ሲታሰብ ደግሞ ጨዋታው በትክክልም ብርቱ ፉክክር የሚስተናገድበት ይሆናል ተብሎ እንዲታሰብ የሚያደርግ ነው።
አሰልጣኝ ስዩም ከበደ አዲሱ አጥቂያቸው ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ልምምድ መመለስ መልካም ዜና ሆኖላቸዋል። ነገም በስብስቡ ውስጥ እንደሚካተት ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪ ሽመክት ጉግሳ ከግል ጉዳይ ሲመለስ ሱራፌል ዳኛቸው ግን አላገገመም። በአርባምንጭ ከተማ በኩል የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን አንድነት አዳነም ከጉዳት አገግሟል።
ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት ይከናወናል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 4 ጊዜ ሲገናኙ ፋሲል ሁለት ጊዜ ፣ አርባምንጭ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ፋሲል 3 ሲያስቆጥር አርባምንጭ አንድ ግብ አስመዝግቧል።
ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)
ሚኬል ሳማኬ
አብዱልከሪም መሐመድ – ያሬድ ባየህ – አስቻለው ታመነ – አምሳሉ ጥላሁን
ከድር ኩሊባሊ – ሀብታሙ ተከስተ
ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – በረከት ደስታ
ፍቃዱ ዓለሙ
አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)
ሳምሶን አሰፋ
ወርቅይታደስ አበበ – በርናንድ ኦቺንግ – አንድነት አዳነ – ተካልኝ ደጀኔ
ሀቢብ ከማል – እንዳልካቸው መስፍን – አንዱዓለም አስናቀ – ፀጋዬ አበራ
በላይ ገዛኸኝ – ኤሪክ ካፓይቶ