የአንደኛ ሊግ ክለቦች ዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት ተዘዋውሯል

የሀገራችን ሦስተኛ የሊግ ዕርከን ውድድር ዕጣ የማውጣት መርሐ ግብር ወደ ወሩ መጨረሻ ተገፍቷል።

በዛሬው ዕለት በጁፒተር ሆቴል እንዲደረግ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ክለቦች ዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓት በአጭር ውይይት ተቋጭቷል። በስብሰባው ላይ ከተገኙት 28 ክለቦች ውስጥ የዳኞች እና የኮሚሽነሮች ክፍያ የፈፀሙት 8 ብቻ መሆናቸውን ተከትሎ ውይይቱ ክፍያቸውን ባልፈፀሙ ቀሪ ክለቦች ዙሪያ ያጠነጠነ ሆኗል።

ስብስባውን ከመሩት አመራሮች ውስጥ የውድድር ዳይሪክቶሬት ዳይሪክተር የሆኑት አቶ ከበደ ወርቁ ክለቦቹ የመፍትሄ ሀሳብ እንዲያመጡ ውይይቱን ክፍት አድርገዋል። በዚህም መሰረት የተለያዩ ሀሳቦች ተንሸራሽረው በመጨረሻም ላልከፈሉ ክለቦች ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጣቸው ውሳኔ ላይ ተደርሷል።

በዚህም መሰረት እስከያዝነው ወር መጨረሻ ክለቦቹ ግዴታቸውን እንዲወጡ ቁርጥ ቀን ተቀምጧል። በወቅቱ ያላጠናቀቁ ክለቦች የሚኖሩ ከሆነ ድልድሉ ፈርሶ የከፈሉት ብቻ ወደ ውድድር እንዲመጡ ይደረጋል። በውሳኔው የተጫዋቾች የመመዝገቢያ ጊዜ ላይ ለውጥ እንደማይኖር ተጠቁሟል።

ከዚህ ውጪ ተሳታፊ ክለቦች ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ለመከላከያ ሰራዊቱ የበከላቸው አስተዋፅዖ እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል። በመጨረሻም የአንደኛ ሊግ ውድድር ፀሀፊነት ቦታ በአቶ አላዩ ቦታ አቶ ዳንኤል ዘለቀ ኃላፊነቱን እንደተረከቡ ተነግሯል።

ያጋሩ