ሪፖርት | ማራኪ ያልነበረው ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል

ከሽንፈት እና አቻ ውጤት በኋላ እርስ በእርስ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ከመጨረሻ ጨዋታቸው ሦስት ሦስት ለውጦችን አድርፈው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ሀዋሳ ከተማዎች አቡዱልባሲጥ ከማልን (ቅጣት) በዳዊት ታደሠ፣ ዮሐንስ ሴጌቦን በመድሃኔ ብርሃኔ እንዲሁም ሄኖክ ድልቢን በበቃሉ ገነነ ሲለውጡ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ ሳምሶን ጥላሁን፣ ባዬ ገዛኸኝ እና መላኩ ወልዴ (ቅጣት) አሳርፈው ደስታ ዋሚሾ፣ ፀጋዬ ብርሃኔ እና ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አካተዋል።

ኳስን በተሻለ ተቆጣጥረው መጫወት የጀመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ባገኙት የቅጣት ምት የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ቢሰነዝሩም የሀዋሳ ከተማ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የራስ ምታት ሆኖባቸው ታይቷል። በተለይ ሀዋሳዎች በሁለቱ መስመሮች ፈጣን ሽግግር ለማድረግ በማሰብ እስከ 12ኛው ደቂቃ ድረስ ብቻ ከአንድም ሦስት ጊዜ ሆሳዕና የግብ ክልል ደርሰው ጥቃት ለመፈፀም ዳድተው ነበር።

ቀስ በቀስ የተመጣጠነ እንቅስቃሴ ማስተናገድ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታም እስከ 37ኛው ደቂቃ ድረስ የግብ ዕድል ሳይፈጠርበት መሐል ሜዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴ ብቻ ተስተውሎበታል። በተጠቀሰው ደቂቃ ግን እጅግ ለግብ የቀረበ ሁነት ተፈጥሮ ነበር። በዚህም መስፍን ታፈሰ ከግራ መስመር መነሻን ያደረገ ኳስ ከኤፍሬም አሻሞ ደርሶት በቀኝ እግሩ በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታውም ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ሀዋሳዎች ከዚህ ሙከራ በፊትም በግማሽ ሰዓት ላይ ፍሬዘር ካሳ መስፍን ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ በተገኘ አጋጣሚ ቀዳሚ ሊሆን ጥረው ነበር።


ወደ ግብ በመድረሱ ረገድ አሁንም ከሀዲያ የተሻሉት ሀዋሳዎች አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት በድጋሜ አስደንጋጭ ሙከራ አድርገው ተመልሰዋል። በዚህም ከደቂቃዎች በፊት ጥሩ ጥቃት የፈፀመው መስፍን በድጋሜ ከኤፍሬው የተሻገረውን ኳስ የሀዲያ ተከላካይ ፍሬዘር ማፅዳት ተስኖት እግሩ ሥር ደርሶ ወደ ግብ ቢመታውም ስሆሆ ሜንሳ በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖበታል። አጋማሹም እምብዛም ሳቢ እንቅስቃሴ ሳይታይበት ያለ ግብ ተጠናቋል።

በአንፃራዊነት በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ብልጫ (የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ) የነበራቸው ሀዋሳዎች የዚህኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አጀማመር ጥሩ አልሆነላቸውም። ገና በ48ኛው ደቂቃም የመሐል ተከላካያቸው ፀጋሰው ድማሙ የመስመር አጥቂው ፀጋዬ ብርሃኑ ላይ በሰራው አደገኛ ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዶባቸዋል። ይህ ቢሆንም ግን በ56ኛው ደቂቃ ያገኙትን የቅጣት ምት በወንድማገኝ ኃይሉ አማካኝነት ግብ ለማድረግ ጥረው ነበር።

የቁጥር ብልጫ ያገኙት ሀዲያዎች በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ መጫወት ጀምረው በ58ኛው ደቂቃ በራሳቸው በኩል የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ አጋጣሚ በፀጋዬ ብርሃኑ አማካኝነት ቢፈጥሩም ቁመታሙ ግብ ጠባቂ መሐመድ ሙንታሪ አምክኖባቸዋል። ቡድኑ ለማጥቃት ፍላጎት ኖሮት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ቢያስገባም ኳስ እና መረብን የሚያገናኝለት ተጫዋች አጥቷል። ሀዋሳ ከተማ ደግሞ በተቃራኒው የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በማስወጣት ወደ ጨዋታው ሲገባ የነበረውን አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥቶ መጫወት ይዟል።

ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩር ደግሞ የአማካይ መስመር ተጫዋቹ አበባየሁ ዮሐንስ ከኢያሱ ታምሩ የተቀበለውን ኳስ ከርቀት ወደ ግብ መትቶት የነበረ ቢሆንም ሙንታሪ ወደ ውጪ አውጥቶበታል። ጨዋታውም ግብ ሳያስተናግድ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

የአቻ ውጤቱን ተከትሎ ከአርባ ደቂቃዎች በላይ በጎዶሎ ተጫዋች የተጫወቱት ሀዋሳ ከተማዎች ከ9ኛ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ አሁንም ከድል ጋር ያልታረቁት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ግን ባሉበት 14ኛ ደረጃ ፀንተው ተቀምጠዋል።