ሪፖርት | ድራማዊ የነበረው የምሽቱ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

ሦስት ፍፁም ቅጣት ምቶች እና ሦስት ቀይ ካርዶችን ያስመለከተን የፋሲል ከነማ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ በ1-1 ውጤት ተቋጭቷል።

ቡድኖቹ ከመጨረሻ ጨዋታቸው አንፃር ባደረጓቸው የአሰላለፍ ለውጦች በፋሲል በኩል ሽመክት ጉግሳ እና ዓለምብርሀን ይግዛው በናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እና ሰዒድ ሀሰን ምትክ ወደ ሜዳ ሲገቡ የአርባምንጭ ከተማው ተካልኝ ደጀኔ በመላኩ ኤሊያስ ተተክቷል።

ጨዋታው ከጅምሩ ብርቱ ፉክክር ማስመልከት የጀመረ ነበር። ፋሲል ከነማዎች ኳስ ይዘው ክፍተትን የመፈለግ አርባምንጮች ደግሞ ከኳስ ጀርባ ሆነው በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ የመግባት ባህሪ ይታይባቸው ነበር። 6ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ጥላሁን በድንገተኛ ጥቃት መሀል ለመሀል የተሰነጠቀለትን ኳስ ተከትሎ ሳጥን ውስጥ የገባው በላይ ገዛኸኝ ላይ በሰራው ጥፋት አርባምንጬች ፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኘም ወርቅይታደስ አበበ የመታው ፍፁም ቅጣት ምት በግቡ ቋሚ ተመልሷል።

ከፍፁም ቅጣት ምቱ በኋላ አርባምንጬች ቀስ በቀስ ከሜዳቸው ወጥተው ከኳስ ውጪ ጫና ወደማሳደር እና የጨዋታውን ሂደት ከአጋማሻቸው የመግፋት ሀሳብ ተንፀብርቆባቸዋል። በዚህም ተጋጣሚያቸው በቅብብሎች ወደ ሳጥናቸው እንዳይቀርብ ማድረግ ሲችሉ የአጋማሹ የተሻለ የሚባለውን ሙከራም አድርገዋል። በዚህም 18ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ አበራ ከበላይ ጋር በመቀባበል ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ወደ ላይ ተነስቷል።

ፋሲሎች በቅብብል ተመስርተው የአርባምንጭን የፊት ጫና ማለፍ ቢሳናቸውም አልፎ አልፌ በቀጥተኛ አጨዋወት ጥቃቶችን ሰንዝረዋል። በሁለት አጋጣሚዎች ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን ቢፈጥሩም የመጨረሻ ቅብብሎቻቸው ጥራት መውረድ የመጨረሻ የግብ ዕድል እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል። በቀሩት ደቂቃዎችም በሁለቱም በኩል ጥሩ ፍልሚያን ብንመለከትም የጨዋታው አጋማሽ ያለከባድ ሙከራዎች የተጠናቀቀ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ከኋላ እና ከፊት መስመራቸው ላይ አስቻለው ታመነ እና ኦኪኪ አፎላቢን ለውጠው ያስገቡት ፋሲሎች ጫን ብለው መጫወት ጀምረዋል። በኳስ ቁጥጥር ብልጫውን የወሰዱት ፋሲሎች ወደ ሳጥን የሚልኳቸው ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችም መታየት ሲጀምሩ 59ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። በረከት ደስታ ከሽመልት ጉግሳ የደረሰውን ኳስ ከአርባምንጭ ተከላካዮች ቀድሞ ለማግኘት ባደረገው ጥረት በአሸናፊ ፊዳ ጥፋት ተፈፅሞበት ፋሲል ፍፁም ቅጣት ምት አግኝቷል። አሸናፊ ፊዳ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ ያሬድ ባየህ አጋጣሚውን ወደግብነት ቀይሮታል።

 

አንድ ተጫዋች የጎደለባቸው አርባምንጬች ከግቡ በኋላ አቻ ለመሆን ወደ ፊት ገፍተው መጫወትን ምርጫቸው ማድረጋቸው ጨዋታውን ከመጀመሪያው ይልቅ ክፍት አድርጎታል። በሁለቱም በኩል ወደ ግብ የመድረስ አዝማሚያ ሲታይ ቆይቶ የአርባምንጮች የቆመ ኳስ ሌላ ፍፁም ቅጣት ምት አስገኝቶላቸዋል። ፍፁም ቅጣት ምቱ ከማዕዘን የመጣውን ኳስ በላይ ገዣኸኝ በግንባር ገጭቶ ያሬድ ባየህ በእጅ በመንካቱ የተሰጠ ሲሆን የዕለቱ ኢንተርናሽናል አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩ ተጫዋቹ በመከራከሩ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ አስወጥተውታል። የአርባምንጩ ኬኒያዊ አጥቂ ኤሪክ ካፓይቶ በበኩሉ አጋጠሚውን 76ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አድርጎ ጨዋታውን ወደ አቻነት አምጥቶታል።

ቀጣዮቹ ደቂቃዎችም ለፋሲል ከነማዎች ሌላ ያልተጠበቀ ቀይ ካርድ ይዘው መጥተዋል። 80ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ተከስተ ወርቅይታደስ አበበን በክርኑ በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ሆኗል። ሆኖም ፋሲሎች ነቅለው በማጥቃት ቀጣዮቹን ሦስት አደገኛ አጋጣሚዎች ፈጥረዋል። 83ኛው ደቂቃ ላይ ኦኪኪ አፎላቢ ቡድኑ ከሰነዘረው የግራ መስመር ጥቃት ከበረከት ደስታ የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውስጥ ሲሞክር ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ሽመክት ጉግሳ በቀኝ በኩል ከቀጥተኛ ኳስ ከበጠባብ አንግል ላይ ከባድ ሙከራዎች አድርገው ሳምሶን አሰፋ አድኖባቸዋል። ቡድኑ በጭማሪ ደቂቃ ደቂቃም በረከት ደስታ ካደረገው የረጅም ርቀት ሙከራ ግብ ለማግኘት ተቃርቦ በድጋሚ ሳምሶን አድኖታል። የፋሲሎች የመጨረሻ ደቂቃ ተደጋጋሚ ጥረት ፍሬ ሳያፈራም ጨዋታው በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ነጥቡን 8 አድርሶ አንድ ደረጃ በማሻሻል 3ኛነትን ሲይዝ መሪነቱን የማስፋት ዕድሉን ያመከነው ፋሲል ከነማም በ10 ነጥቦች አንደኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።