የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 1-1 አርባምንጭ ከተማ

በአስገራሚ ክስተቶች ታጅቦ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀው ጨዋታ መጠናቀቅን ተከትሎ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ስለጨዋታው

“የባለፈው ጨዋታቸውን ታሳቢ በማድረግ ዝግጅቶችን አድርገን ነበር ፤ ይህን ሂደት በተረጋጋ መልኩ ኳሱን ተቆጣጥረን ለመውጣት ነበር አስበን የነበረው። በመጀመሪያ ያ አልሆነም፤ በሁለተኛው አጋማሽ ለማረም የሞከርነው ተረጋግተን ሳንቻኮል ለመውጣት የተጫዋች ለውጥም አድርገን ነበር። አስቻለው ለኳስ ምስረታ የተመቸ ነው። ኦኪኪን ታሳቢ ያደረጉ ኳሶችን በአማራጭነት ለመጠቀም ሞክረናል፤ ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ ባንሆንም። የእነ ሀብታሙ በቀይ መውጣት የሚሰርቅህ ነገር አለ። ያንንም ተቋቁመን ለመጫወት ሞክረናል። ቢሆንም በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተገኘው ውጤት መጥፎ አልነበረም። በዲሲፕሊን ረገድ የወጡት ተጫዋቾች ለሌሎች መማርያ በማድረግ የምናሻሽለው ይሆናል።”

በመጀመሪያው አጋማሽ ስለነበራቸው ደካማ እንቅስቃሴ

“ከፍ ያለ ጫና በማሳደራቸው ከሜዳችን መውጣት አልቻልንም፤ ይህንንም ለመስበር ተደጋጋሚ ኳሶች ወደ እነሱ ሜዳ ይዘን መውጣት እንደሚገባን እዛ በሚገኙ ሁለተኛ ኳሶች ተፅዕኖ ለመፍጠር ነበር ያሰብነው። ነገርግን አልተካልንም። በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሻለ ነገር ቢኖርም የተጫዋቾች መውጣት ተፅዕኖ ፈጥሮብናል።”

ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ስለመጣላቸው

“አሁንም ከላይ ነው ያለነው፤ ውድድሩ የ30 ጨዋታ ነው። ነጥብም ጥለን ቢሆን አሁንም ከላይ ነው ያለው የታመሙት ልጆች እየመጡ ነው። በመሆኑም ፋሲል አሁንም በተከታታይ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት በከፍተኛ ተነሳሽነት ላይ እንገኛለን።”

መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ስለ ቀይ ካርዶቹ

“ሁለቱ በፍፁም ቅጣት ምት አጋጣሚዎች እንዲሁም አንዱ በክርን በመማታቱ የተሰጡ ናቸው። የእኛ ቡድን ከፍተኛ ጫናን ፈጥሮ የሚጫወት ቡድን ነው። ይህ አጨዋወት ደግሞ በባህሪው ከፍ ያለ ፍጥነት ስለሚታከልበት ትንሽ ዱላ የሚመስል ነገር አለው።”

በሁለተኛው አጋማሽ ስለመቸገራቸው

“እነ ኦኪኪ ከገቡ በኃላ በተወሰነ መልኩ ቀጥተኛ አጨዋወትን ሲጠቀሙ ነበር። የእኛም ልጆች በተወሰነ መልኩ መረጋጋት ተቸግረው ነበር በዚህ እነሱ እድሎችን ፈጥረውብን ነበር።”

ቡድኑ ስላሳየው መሻሻል

“በሚጎሉን ነገሮች ላይ እንሰራለን የራሳችን የሆነ መልክ አለን በሚጎሉን ነገሮች ላይ እየጨመርን እና እያሻሻልን እንቀርባለን ልጆቹም ይበልጥ እየተዋሀዱ ሲመጡ እያሳደግነው እንመጣለን።”

የዛሬው ውጤት በቀጣይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ

“ፋሲል ጠንካራ ቡድን ነው ባለፈው ከባህርዳር ጋር የነበረው ጨዋታችን ነጋችን ብሩህ እንደሆነ ያሳያል።ከዚህ በላይ ሰርተን በየጨዋታው ሶስት ነጥብ ለመያዝ እንሰራለን።”