ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

በነገው ቀዳሚ የሊጉ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በአራተኛው ሳምንት ድል ማስመዝገብ የቻሉ ሁለት ቡድኖችን የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ ብርቱ ፉክክርን እንደሚያስመለክተን ይታሰባል። ውድድሩን በድል ቢጀምሩም በሲዳማ ሰፊ ሽንፈት የገጠማቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ከዛ ወዲህ ጥሩ መሻሻል አሳይተው ጅማ አባ ጅፋርን በሰፊ ግብ ልዩነት በመርታት ለነገው ጨዋታ ደርሰዋል። ከሁለት የአቻ ውጤቶች ውጪ ነጥብ ያልነበራቸው ወልቂጤዎችም ሀዋሳ ከተማ ላይ የመጀመሪያ ድላቸውን ማሳካት ችለው ነበር። በመሆኑም ቡድኖቹ ነገ በጥሩ የማሸነፍ ሞራል ላይ ሆነው ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ከድሎቹ ባሻገር ቡድኖቹ ለማጥቃት የጨዋታ ዕቅድ ቅድሚያ ሰጥተው መታየታቸው የነገውን ፍልሚያ ተጠባቂ ያደርገዋል። ከመዋቅር አንፃር ግን በመጨረሻ ጨዋታቸው የተለያየ ባህሪን አሳይተውን ሁለቱም ውጤታማ ሆነው ነበር። ድሬዎች በጊዮርጊሱ የአቻ ጨዋታ የተጠቀሙትን አጨዋወት እና ስብስብ ሳይቀይሩ (ከታች በግምታዊ አሰላለፍ ላይ የተመለከተው) በመግባት የተሻለ ውህደትን አሳይተዋል። ነገም በተመሳሳይ አኳኋን ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። በወልቂጤ በኩል ደግሞ ባለፉት ጨዋታዎች ፊት መስመሩ ላይ ያሉትን ተጫዋቾች በመለዋወጥ ሲጠቀም ቆይቶ ወደ 4-4-2 ዳይመንድ በተጠጋ የቅርፅ ለውጥ ወደ ሜዳ በመግባት አንድ ግብ እና ሦስት ነጥቦችን ይዞ መውጣት ችሏል። በእነዚህ ሁለት መንገዶች የተቃኙት የጨዋታ ዕቅዶች ነገ ሲገናኙ ማን ውጤታማ ይሆናል የሚለውን ከጨዋታው የምንጠብቅ ይሆናል።

ድሬዳዋ በጅማው ጨዋታ ተፈትኗል ባይባልም የመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት ሚና በተለይም በእንየው ካሳሁን በኩል የተሳካ ነበር። በዚሁ አቅጣጫ የወልቂጤው ረመዳን የሱፍ የማጥቃት ባህሪ ያለው መሆኑን ስናስብ ደግሞ ነገ በቦታው የሚኖረው ፍልሚያ እጅግ ወሳኝ እንደሚሆን እንረዳለን። ከዚህ ባለፈ የጋዲሳ መብራቴ እና አብዱለጢፍ መሀመድ የማጥቃት ኃይል ለቡድኑ የኳስ ፍሰት የማጥቃት መዳረሻ ከመሆኑ ባለፈ የማማዱ ሲዲቤ ወደ ግብ አስቆጣሪነት መምጣት ተጨማሪ ኃይል እንደሚሆን ይታመናል። ሆኖም ከጅማ በተለየ አማካይ ክፍል ላይ ብልጫ ለመውሰድ ፍላጎት እና የተሻለ ጥራት ያለው ተጋጣሚ ጋር ሲገናኝ በቂ ኳሶችን ወደ አጥቂዎቹ ያደርሳል ወይ የሚለው ነጥብ የድሬን የነገ የበላይነት የመወሰን አቅም ይኖረዋል።

በወልቂጤ በኩል የጌታነህ ከበደ የኋልዮሽ እንቅስቃሴ መሀል ላይ ብልጫን ለመውሰድ እና የቅብብል አማራጮችን ለመፍጠር ሲረዳው ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪ ከአማካዩ አብዱለከሪም ወርቁ ግብ ማግኘቱም የግብ ምንጭ አማራጩን በማስፋቱ በኩል በበጎ ጎን የሚታይ ነው። ሆኖም ከተከላካይ ፊት ባለው ቦታ ላይ የመጀመሪያ ሁለት ተመራጮቹን በዳሳት እና ቅጣት ማጣቱ የቁጥር እና የቁጥጥር ብልጫ እንዳይወሰድበት ያሰጋዋል። ይህንን ተንተርሶም አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ዳግም ሌላ ያልተጠበቀ ቅርፅ ይዘው ወደ ሜዳ መግባት ወይም ቦታውን ሰው በሰው ተክተው የጌታነህን ነፃ ሚና በማጉላት መሀል ሜዳ ላይ እጅ ላለመስጠት እንደሚጥሩ ይገመታል። ከሁሉም በላይ ግን መፍትሄያቸው በድኑ ከፊት የሚኖረውን ስልነት እንዳይቀንሰው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ድሬዳዋ ከተማ አጥቂው ሄኖክ አየለ ከጉዳት የተመለሰለት ሲሆን በአንፃሩ ዳንኤል ኃይሉን ደግሞ በጉዳት ያጣል። በወልቂጤ በኩል ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ በቅጣት ሀብታሙ ሸዋለም እና አቡበከር ሳኒ በጉዳት ጨዋታው ሲያልፋቸው ቀለል ያለ ልምምድ የጀመረው ዮናስ በርታም ለነገ አይደርስም።

ጨዋታው በፌደራል ዳኛ ብርሀኑ መኩሪያ የመሀል ዳኝነት ይመራል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– አምና በተከናወኑት የመጀመሪያ ዓመት ሁለት ግንኙነቶቻቸው ወልቂጤ ከተማ 3-1 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 2-1 ማሸነፍ ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

እንየው ካሳሁን – መሳይ ጳውሎስ – አውዱ ናፊዩ – ሄኖክ ኢሳይያስ

ብሩክ ቃልቦሬ – ዳንኤል ደምሴ

ጋዲሳ መብራቴ – ሙኸዲን ሙሳ – አብዱለጢፍ መሀመድ

ማማዱ ሲዲቤ

ወልቂጤ ከተማ (4-4-2 ዳይመንድ)

ስልቪያን ግቦሆ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

አብርሀም ታምራት

ያሬድ ታደሰ – በኃይሉ ተሻገር

አብዱልከሪም ወርቁ

ጌታነህ ከበደ – እስራኤል እሸቱ