ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ

የአምስተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ መርሐ-ግብሮች ነገም ሲቀጥሉ የዕለቱን ሁለተኛ ጨዋታ በሚከተለው መልኩ ቃኝተነዋል።

በሁለተኛ ሳምንት ጅማ አባጅፋርን አንድ ለምንም ካሸነፈ በኋላ ዳግም ሦስት ነጥብ ማሳካት ያልቻለው አዳማ ከተማ ከሽንፈት እና ከአቻ ውጤቶች በኋላ ከድል ጋር ለመገናኘት ነገ ታትሮ እንደሚጫወት ይታመናል።

በአራቱም የሊጉ ጨዋታዎች ቢያንስ በሁለት የሜዳ ክፍሎች ላይ ለውጥ እያደረጉ ሲጫወቱ የታዩት አዳማዎች የተረጋጋ ቡድን ያላቸው አይመስልም። በተለይ ደግሞ ቡድኑ የማጥቃት አጨዋወቱን በጥሩ መልኩ ያዋቀረ አለመሆኑ በአራት ጨዋታዎች ሁለት ጎሎችን ብቻ (አንዱ በቅጣት ምት) ተጋጣሚ ላይ እንዲያስቆጥር ያደረገው ይመስላል። እርግጥ በስብስቡ ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች ጥራት በአሳሳቢ ደረጃ የወረደ አለመሆኑ ሲታሰብ ደግሞ አሠልጣኙ የውህደት ሥራዎችን መስሪያ ጊዜ ሲያገኙ ክፍተቱ የሚሸፈን እንደሆነ ያመላክታል። ምንም ቢሆን ምንም ግን በአሁኑ ሰዓት ከወራጅ ቀጠናው ቦታ በሁለት ደረጃዎች ብቻ ከፍ ብሎ የሚገኘው ቡድኑ ጨዋታዎች ላይ የሚኖረውን ብልጫ በውጤት በማሳጀብ ማጠናቀቅ ካልቻለ ከበላዩ የሚገኙት ክለቦች እየራቁት ይሄዳሉ። ይህ እንዳይሆን ደግሞ በጥሩ ተነሳሽነት ላይ የሚገኘውን አዲስ አበባን በመርታት ወደ አሸናፊነት መንገድ መግባት የግድ ይለዋል።

ከላይ እንደጠቀስነው ቡድኑ ግቦችን የማስቆጠር ችግር ቢኖርበትም ከወገብ በላይ የሚገኙት ተጫዋቾቹ ፍጥነት በተደጋጋሚ ለተጋጣሚ ቡድኖች ፈተና ሲሆን ይታያል። በተለይ ተጫዋቾቹ ከተከላካይ ጀርባ በመሮጥ የተዋጣላቸው ናቸው። ነገም ይህንን ባህሪ በአዲሱ የሊጉ ክለብ ላይ የሚያሳዩት ከሆነ እና የአጨራረስ ብቃታቸውን የሚያስተካክሉ ከሆነ ሊጠቀሙ ይችላሉ። ከዚህ ውጪ ግን በጥሩ ተነሳሽነት ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ያሸነፈውን የአዲስ አበባን ታታሪነት የተሞላበት አጨዋወት ፉርሽ ማድረግ የግድ እንደሚላቸው ይታመናል።

ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሁለቱን በድል ሁለቱን ደግሞ በሽንፈት ያጠናቀቁት አዲስ አበባ ከተማዎች ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን አዳማ ከተማ ላይ ለመቀዳጀት ተዘጋጅተው ጨዋታውን እንደሚቀርቡ ይገመታል።

በምክትል አሠልጣኙ ደምሰው ፍቃዱ እየተመራ አዎንታዊ ውጤት ማስመዝገብ የጀመረው የመዲናው ክለብ አዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ጨዋታዎች የታየበት መነቃቃት አስገራሚ ነው። በተለይ በከፍተኛ የፍላጎት ደረጃ በመጫወት ተጋጣሚን ከኳስ ጋር እና ከኳስ ውጪ በጥሩ ሁኔታ ሲያስጨንቁ ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ የወቅቱን የሊጉን አሸናፊ ፋሲል ገጥመው በመጀመሪያው አጋማሽ ያሳዩት ሜዳን አካሎ የመጫወት ብቃት ነገ የሚደገም ከሆነ አዳማ ከተማ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። የመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አምልጦት በአራተኛው ጨዋታ የተሰለፈው ኤሊያስ አህመድ ደግሞ የቡድኑ የልብ ምት እንደሚሆን ያሳየበትን ቀን በዕለቱ ማሳለፉ ይታወሳል። ምናልባት ተጫዋቹ በወጥነት የነገውን ጨዋታ ከቀረበ ደግሞ የቀድሞ ክለቡ የተጫዋቹን ብቃት ማምከኛ ዘዴ መዘየድ የግድ ይለዋል።

የኋላ መስመሩን ጥምረት በየጨዋታው ሲቀያይር የሚታየው አዲስ አበባ ከአራቱ ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረው በአንዱ ብቻ ነው። ይህ የግል ብቃት እንዲሁም ቡድናዊ መዋቅር የሚጠይቀው የተከላካይ መስመር ደግሞ ከጨዋታ ጨዋታ አንፃራዊ እድገት እያሳየ ቢመጣም የተረጋጋ መሆን ይጠበቅበታል። ነገ ደግሞ ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ውጤት ሳያገኝ የመጣው አዳማ ምላሽ ለመስጠት ሊያደርግ ከሚችለው ጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ አንፃር በጥሩ ሁኔታ መቃኘት እንዳለበት ይታመናል።

በአዳማ ከተማ በኩል ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የሌለ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የሺዋስ በለው፣ ፈይሰል ሙዘሚል እና ቴዎድሮስ ሀሙን በጉዳት ምክንያት የማያሰልፉ ይሆናል።

ይህንን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በዓምላክ ተሰማ የሚመሩት ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በፕሪምየር ሊጉ 2009 ላይ ተገናኝተው የነበረ ሲሆን አዳማ ከተማ 2-1 እና 3-1 ማሸነፍ ችሎ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ሴኩምባ ካማራ

ሚልዮን ሰለሞን – አሚን ነስሩ – ቶማስ ስምረቱ – ደስታ ዮሐንስ

ኤልያስ ማሞ – ዮሴፍ ዮሃንስ – አማኑኤል ጎበና

አሜ መሐመድ – ዳዋ ሆቴሳ – አብዲሳ ጀማ

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል ተሾመ

ልመንህ ታደሰ – አሰጋኸኝ ጽጥሮስ – ሳሙኤል አስፈሪ – ሙለቀን አዲሱ

ኤሊያስ አህመድ – ቻርለስ ሪባኖ – ያሬድ ሀሰን

እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ አዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን

ያጋሩ