ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎች ጅማ አባጅፋርን ሦስት ለአንድ ሲረቱ የተጠቀሙበትን ቋሚ አሰላለፍ በዛሬው ጨዋታም ተጠቅመዋል። በተመሳሳይ ከድል ማግስት ለዛሬው ጨዋታ የተዘጋጁት ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ በሀዋሳው ጨዋታ ሁለት ቢጫ ካርድ አይቶ ከሜዳ የወጣው ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስን ብቻ በአብርሐም ታምራት ለውጠው ጨዋታውን ቀርበዋል።
ፈጠን ባለ የማጥቃት ምልልስ እንቅስቃሴ ውስጥ ሆኖ በጀመረው ጨዋታ ድሬዳዋዎች አንፃራዊ ብልጫን ወስደው ታይተዋል። በአብዱለጢፍ መሀመድ መስመር (ቀኝ) አጋድለውም የግብ አጋጣሚዎች ለመፍጠር የሚያስችሉ ኳሶችን ወደ ሳጥን ሲያደርሱ ነበር። በጨዋታው 10ኛው ደቂቃ ላይ ግን እስራኤል እሸቱ ወደ ግራ ካደላ ቦታ ላይ አክርሮ የመታው ኳስ የወልቂጤ ከተማ ቀዳሚው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሆኗል።
12ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ጌታነህ ከበደ ያሻማዋል ተብሎ የተጠበቀውን ቅጣት ምት በቀጥታ በመምታት ወልቂጤ ከተማን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ተቆጥሯል። ከጎሉ ሁለት ደቂቃዎች በኋላም ወልቂጤዎች በፈጣን ጥቃት ሳጥኑ አቅራቢያ ደርሰው እስራኤል ዒላማውን ያልጠበቀ ከባድ ሙከራ አድርጓል። ወልቂጤዎች ለተወሰኑ ደቂቃዎች ነቃ ብለው በተጋጣሚያቸው አጋማሽ ላይ መቆየት ችለዋል። በሂደት ጫናውን ማርገብ የጀመሩት ድሬዳዋዎችም ማማዱ ሲዲቤን ያማከሉ ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ፊት በመላክ ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል።
በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ እየተሻሻሉ የመጡት ተመሪዎቹ ድሬዳዋዎች በ33ኛው ደቂቃ ሔኖክ ኢሳይያስ ከሳጥን ውጪ በግራ እግሩ አክርሮ በመታው ኳስ አቻ ለመሆን ጥረዋል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በተቃራኒ አቅጣጫ የተሰለፈው እንየው ካሳሁን ሌላ ጥሩ ዕድል አግኝቶ ነበር። በዚህ ደቂቃም ተጫዋቹ ከዳንኤል ደምሴ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ቢመታውም ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። አሁንም ወልቂጤ የግብ ክልል በመድረስ በሙኸዲን ሙሳ አማካኝነት ሁለት ተጨማሪ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ኳስ እና መረብን ሳያገናኙ አጋማሹ ተገባዷል።
ገና የሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተጀመረ በሰከንዶች ውስጥም ድሬዳዋዎች በቁመታሙ አጥቂያቸው ሲዲቤ እና የመስመር ተጫዋቹ ጋዲሳ አማካኝነት በቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረዋል። በመጀመሪያው የጨዋታ ደቂቃዎች የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ጥሩ የነበሩት ወልቂጤዎች በ50ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ሊያደርጉ ነበር። በዚህም ከመሐል የተሻገረውን ኳስ ተከላካዩ መሳይ እና ግብ ጠባቂው ሲልቪያን ሳይግባቡ ቀርተው ከሳጥኑ ጫፍ ኳስ ያገኘው እስራኤል ተገልብጦ (በመቀስ ምት) ወደ ግብ በመምታት ሊቀጣቸው ነበር።
አሁንም ጫና ማሳደራቸውን ያላቆሙት ድሬዎች በ68ኛው ደቂቃ ተስፋዬ ነጋሽ ጥፋት ሰርቶ የተገኘውን የቅጣት ምት በማማዱ ሲዲቤ አማካኝነት ወደ ግብ ልከውት የነበረ ሲሆን ኳሱ ግን ለጥቂት ተከላካዮች ጨርፈውት ወደ ውጪ ወጥቷል። በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ ላለማጣት ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥተው መጫወት የቀጠሉት ወልቂጤዎች በመልሶ ማጥቃት እና በረጃጅም ኳሶች አሁንም አደገኛ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ነበር። በ74ኛው ደቂቃም በረጅሙ የተላከውን ኳስ አሁንም መሳይ እና ሲልቪያን ሳይግባቡ ቀርተው አብዱልከሪም ወርቁ አግኝቶት ለበሀይሉ ተሻገር ቢያቀብለውም አማካዩ በነበረው የወረደ ዝግጁነት መልካሙን አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
አሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ቢያንስ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን አከታትለው በማስገባት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ቡድናቸው በሙሉ ሀይሉ እንዲያጠቃ ቢያረጉም ውጥናቸው ሳይሰምር ቀርቷል። በተለይ ደግሞ ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመሩት ደቂቃዎች በአቤል ከበደ አማካኝነት እጅግ ጥሩ ኳስ ወደ ግብ ቢልኩም ዮናስ እና የግቡ ቋሚ አምክኖታል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም አብዱረህማን ሙባረክ ከሳጥኑ ጫፍ ሌላ ጥቃት ሰንዝሮ ነበር። ጨዋታው ግን በወልቂጤ ከተማ አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።
በዓመቱ ያገኙትን የድል ቁጥር ወደ ሁለት ከፍ ያደረጉት ወልቂጤ ከተማዎች ነጥባቸውን 8 በማድረስ በጊዜያዊነት ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል። በተቃራኒው ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ እስካሁን የሰበሰቧቸውን 7 ነጥቦች በመያዝ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ሸርተት ብለዋል።