የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 0-1 ወልቂጤ ከተማ

የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ተካታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ- ድሬዳዋ ከተማ

ጨዋታው እንዳሰቡት ስለመሄዱ

እንደዛ ማለት ይቻላል። ተጭነን ለመጫወት ሞክረናል። ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ፈጥረናል። ግብ አካባቢ ስንደርስ ችግሮች ነበሩብን ፤ በቆመ ኳስ ተሸንፈን ልንወጣ ችለናል። ነገር ግን በዚህ ሳምንት ባሸነፍንበት ጨዋታ ዛሬ ብንሸነፍበትም የምንጫወትበት መንገድ ተመችቶኛል። በተለይ ከዕረፍት በፊት ብዙ ኳሱን አልተቆጣጠርንም። ዝም ብሎ ረጅም ኳስ ነበር የነበረው። በኋላ ግን አስተካክለን ለመምጣት ሞክረናል። ግን አሁንም ጥድፊያዎች ነበሩ በጣም። የማጥቃት ወረዳው ላይ ስንደርስ መረጋጋት አልቻልንም ነበር።

ዕድሎችን ስለማባከናቸው

በቶሎ ስለተቆጠረብን ነው መሰለኝ ጥድፊያዎች ነበሩ። ዘጠና ደቂቃ ረጅም ሰዓት ነው ተረጋግተን መጫወት ብንችል የተሻለ የሚሆንበት ዕድል ነበር። ብንሸነፍም የጎል ዕድል የፈጠርንበት መንገድ ጥሩ ነበር።

ስለፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄ

ዳኛው ባለፈው እኛን ሲያጫዉት የስድስት ወር ቅጣት ተላልፎበት ነበር። ትንሽ ጫን ሊለን ሞክሯል። እንጂ ግልፅ የሆነ ዕድል ስለነበር ያንን መጠቀም ነበረብን። ዳኛው ይህንን ሊከለክለን አይገባም ነበር። በዛ የተወሰነ ቅር ብሎናል። ከዛ ውጪ ግን በተጫዋቾቼ እንቅስቃሴ ደስ ተሰኝቻለሁ።

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

ጨዋታው እንደተመለከታችሁት ክፍት ነበር። መጨረሻ ላይ ውጤታችንን ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አፈግፍገን ተጫውተናል። ወደ ፊት ደግሞ ይህ ነገር አይደገምም። ሁለት ሦስት ጎል አግብቶ በራስ መተማመን መጫወቱን ደግሞ ወደ ፊት እናዳብረዋለን።

ተከታታይ ድሉ ስለሚፈጥረው ለውጥ

ከዚህ በፊትም ይህንን ቡድን ጠብቁት ብዬ ነበር። ምክንያቱም በፈለግነው አቀራረብ ለመጫወት የሚያስችሉ ተጫዋቾች አሉን። ያንን ወደፊት አጎልብተን ነገሮች ከተስተካከሉ ጥሩ ይሆናል። ለተጫዋቾቹ መሟላት አለበት የምለው ነገርም አለ። ይሄን ሁሉ መስዕዋትነት የወልቂጤን ማልያ ለብሰው እየከፈሉ ነው ፤ እኔም የወልቂጤን ማልያ አግኝቻለሁ። ስለዚህ ወደፊት ፉክክር ውስጥ ለመግባት ነው ሀሳባችን።

ያጋሩ