አዲስ አበባ ከተማዎች እየመሩ እስከመጨረሻው የዘለቁበት ጨዋታ በአብዲሳ ጀማል የመጨረሻ ደቂቃ ግብ 1-1 ተጠናቋል።
አዳማ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ አራት ለውጦችን ሲያደርግ አቡበከር ወንዱሙ ፣ ፍራኦል ጫላ ፣ ታደለ መንገሻ እና አሚኑ ነስሩ የአብዲሳ ጀማል ፣ አሜ መሀመድ ፣ ዮሴፍ ዮሀንስ እና ጀሚል ያዕቆብ ቦታ በመያዝ ጨዋታውን ጀምረዋል። አዲስ አበባዎች ግን አሸናፊ ስብስባቸውን ሳይለውጡ ፋሲልን በገጠመበት ስብስብ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
በተመጣጣኝ ፉክክር ጅማሮውን ያደረገው ጨዋታ በጊዜ ግብ ለማስተናገድ ተቃርቦ ነበር። አዳማ ከተማዎች 4ኛው ደቂቃ በግራ በኩል በሰነዘሩት ጥቃት ፍራኦል ጫላ ከወደ ግራ የሳጥኑ ክፍል የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሲመታው የግቡ ቋሚው መልሶበታል። የተመለሰውን ኳስ ደግሞ በሩቁ ቋሚ ራሱን ነፃ አድርጎ ለነበረው አቡበከር ወንድሙ አሻምቶለት አቡበከር በግንባሩ ኳሱን ወደ ግብ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖታል።
በአዳማዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የቀጠለው ጨዋታ ቡድኖቹ ተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ግራ አድልተው ጥቃቶችን ለመሰንዘር ጥረዋል። ቀጣዩ ከባድ ሙከራ በአዲስ አበባ በኩል ሲታይ 16ኛው ደቂቃ ላይ ከኋላ ከቻርለስ ሪባኑ በረጅሙ የታላከን ኳስ ቶማስ ስምረቱ በግንባሩ ለግብ ጠባቂው ሊያደርስ ሲሞክር ሪችሞንድ ኦዶንጎ በመሀል ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር።
ጨዋታው አዲስ አበባዎች ወደ አዳማ ሳጥን ገፍተው የሄዱባቸው አጋጣሚዎች ቢያዩም አብዛኛው እንቅስቃሴ በሁለቱ ሳጥኖች መሀል የቆየ ነበር። ነገር ግን ደቂቃዎች ሲገፉ አዳማዎች ሁለት ጥሩ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር። 30ኛው ደቂቃ ላይ ፍራኦል ጫላ በግሩም ሁኔታ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ ከቅርብ ርቀት ቢሞክርም ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው እና በዕድሜ ዕርከን ውድድሮች ድንቅ አቋም አሳይቶ ወደ ሊጉ የመጣው ታዳጊው አጥቂ ፍራኦል 41ኛው ደቂቃ ላይም ከሳጥን ውጪ በድንቅ ሁኔታ አክርሮ የመታው ኳስ በዳንኤል ብቃት ነበር ግብ ከመሆን የዳነው።
አዲስ አበባዎች በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት ይጠቀሙበት የነበረው የፍፁም ጥላሁን መስመር በመጨረሻ ፍሬ አፍርቶላቸዋል። 44ኛው ደቂቃ ላይ አሚን ነስሩ በፍፁም ጥላሁን ላይ በሰራው ጥፋት ምክንያት አዲስ አበባዎች ፍፁም ቅጣት ምት ሲያገኙ ፍፁም ራሱ በመምታት አስቆጥሯል።
በሁለተኛው አጋማሽ አብዲሳ ጀማልን ለውጠው ያስገቡት አዳማዎች እንደመጀመሪያው ሁሉ በከባድ ሙከራ ጀምረዋል። 49ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከግራ መስመር ካደላ ቦታ በድንቅ ሁኔታ ተጫዋቾችን በማለፍ ወደ ውስጥ ይዞ በመግባት ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም ያደረገው ያለቀለት የግብ ሙከራ በዕለቱ ልዩ የነበረው ዳንኤል አውጥቶበታል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች አዲስ አበባዎች ወደ ኋላ ቀረት ማለት ሲጀምሩ አዳማዎች የመጫን ዕድልን አግኝተዋል 62ኛው ደቂቃ ላይም ቶማስ ስምረቱ ከማዕዘን የተሻገረን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ወጥቶበታል። 68ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተቀይረው የገቡት አሜ መሀመድ እና ኤልያስ ማሞ በአቀባይነት እና በሞካሪነት የተጣመሩበት የሳጥን ውስጥ ሙከራም በዳንኤል ድኗል።
አዳማዎች ተደጋጋሚ ሙከራቸውን አላቋረጡም። 76ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሄቴሳ ከሚሊዮን ሰለሞን የደረሰውን ኳስ በመቀስ ምት ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ሙከራ ለዓይን ሳቢ ነበር። አዲስ አበባዎች የሚቃጣባቸውን ጥቃት በማቋረጥ በረጅሙ በማራቅ ወደ ሪችሞንድ ኦዶንጎ ማድረሳቸውን ቀጥለዋል። ወደ ፍፃሜው ላይ የአዲስ አበባ የሞት ሽረት መከላከል ጎልቶ ሲታይ አዳማዎች በዳዋ ሆቴሳ የተለመዱ ሁለት አደገኛ ቅጣት ምቶች እንዲሁም ከሳጥን ውስጥ የተዳረገ ሙከራ ግብ ለማግኘት ቢቃረቡም ዳንኤል ተሾመ የሚቀመስ አልሆነም። ስድስት ጭማሪ ደቂቃዎችን ያስተናገደው ጨዋታ ግን የአዲስ አበቤዎቹን ሙሉ ነጥብ የማግኘት ተስፋ አምክኗል። ሰባተኛው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ከሌላ የዳዋ ሆቴሳ ቅጣት ምት መነሻነት ተቀይሮ የገባው አብዲሳ ጀማል የተጨራረፈውን ኳስ ወደ ግብነት ለውጦ አዳማ አንድ ነጥብ እንዲያሳካ አድርጓል።
ውጤቱን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ ከነበረበት ዘጠነኛ ደረጃ ወደ ስድስተኝነት ከፍ ሲል አዳማ ከተማም በአንድ ከፍ ብሌ 11ኛ ሆኗል።