ኢትዮጵያ ቡና ልምምድ ያልተገኘውን ተጫዋች ወደ አዲስ አበባ ልኳል

በአምስተኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የፊታችን ማክሰኞ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር የሚያደርገው ኢትዮጵያ ቡና አንድ ተጫዋቹን ወደ አዲስ አበባ ልኳል።

በዘንድሮ ዓመት ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት የተቸገረው ኢትዮጵያ ቡና በቀጣይ ማክሰኞ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ወሳኝ ጨዋታውን ከማድረጉ አስቀድሞ በዛሬ የልምምድ መርሐግብር ላይ አንድ ተጫዋች ሳይገኝ ቀርቷል። በልምምድ ወቅት ያልተገኘው ተጫዋች አማካይ ታፈሰ ሰለሞን ሲሆን አሰልጣኝ ካሣዬ በሁኔታው ደስተኛ በላመሆን ”አዲስ አበባ በመሄድ ለክለቡ ፅህፈት ቤት ሪፖርት አድርግ” በማለት መላካቸውን ሲታወቅ ታፈሰ ሰለሞንም በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ እንደሚገኝ አረጋግጠናል።

ታፈሰ በልምምድ ያልተገኘው ህመም አጋጥሞት እንደሆነ ገልፆ ነገ ሪፖርት ካደረገ በኃላ ወደ ሀዋሳ እንደሚመለስ ነግሮናል። በአንፃሩ በክለቡ በኩል እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ የዲሲፕሊን ግድፈት በመፈፀሙ ወደ አዲስ አበባ መላኩን እና ክለቡ ከቀረበለት ሪፖርት በመነሳት የሚወስነው ውሳኔ እንደሚኖር ሰምተናል።

ያጋሩ