ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ መከላከያ

ጠንካራ ፉክክር እንደሚደረግበት የሚጠበቀውን የጣና ሞገዶቹን እና የጦረኞቹን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ሊጉን አዲስ አበባ ከተማን ሦስት ለምንም እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕናን አንድ ለባዶ በማሸነፍ የጀመረው ባህር ዳር ከተማ ቀስ በቀስ እየተንሸራተተ ካለው ውጤቱ ለማገገም እና የደረጀ ሰንጠረዡ አናት አካባቢ ለመዝለቅ ጠንክሮ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታመናል።

በቡድኑ ውስጥ ካለው የስብስብ ጥራት መነሻነት ብዙዎች ባህር ዳርን ለዋንጫ ተፎካካሪነት ቢያጩትም ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ግን ቡድኑ ይሄንን ነገር በሜዳ ላይ ሲያስመለክት አልነበረም። በተለይ ደግሞ በማጥቃቱ ረገድ ቡድኑ ፍጥነት አልባ ሆኖ በመቅረቡ ተጋጣሚ ቡድኖች እንዳይቸገሩ ያደረገ ይመስላል። እርግጥ አሁንም ቡድኑ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ስላሉት በቡድናዊ መዋቅር የማጥቃት ስትራቴጂውን በመልካም ሁኔታ ቃኝቶ እንዲሁም ፍጥነትን ጨምሮ ከገባ መከላከያዎች ሥራዎች ሊበዛባቸው ይችላል።

ኳስን በመቆጣጠር ረገድ የማይታሙት ባህር ዳሮች በአርባምንጭ ሁለት ለአንድ ሲሸነፉ የኳስ ቁጥጥራቸው ቀጥተኝነት፣ ፍጥነት እና ዓለማ አልነበረውም ነበር። የነበሩት ዓላማ ቢስ የኳስ ቅብብሎች ምናልባት ነገ ከተቀረፉ በራሳቸው ሜዳ አፈግፍገው እንደሚጫወቱ የሚገመተው መከላከያዎች ሊቸገሩ ይችላሉ። ከምንም በላይ ደግሞ በባህር ዳር ቡድን ውስጥ የሚገኙት ከወገብ በላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ወቅታዊ ብቃት የነገው ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪ ሊሆን ይችላል። እንደተገለፀው መከላከያ የጨዋታ መንገዱን በመከላከሉ ረገድ ቃኝቶ ሊመጣ ስለሚችል የግል ተጫዋቾች ብቃት ደግሞ ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ እንደ ፍፁም፣ ፎዐድ እና ማውሊ አይነቶቹ የሚያንሱ አይመስሉም።

በሊጉ ዝቅተኛ ግብ ተጋጣሚ ቡድን ላይ ካስቆጠሩት ሰበታ እና ጅማ በመቀጠል የሚገኘው መከላከያ (አዳማ፣ ሀዲያ እና ቡና ጋር በመሆን) ያለፉት ጨዋታዎች ላይ ደግሞ ይበልጥ የሥልነት ችግር ተስተውሎበታል። እርግጥ ቡድኑ በጨዋታ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን የሚፈጥር ባይሆንም በጊዮርጊሱ ጨዋታ ደግሞ በአንፃራዊነት ከግብ ጫፍ እየደረሰ አጋጣሚዎችን ሲያመክን ነበር። በተለይ በረጃጅም ኳሶች እና በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚጥረው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ዳግም ለሦስት ነጥብ ጋር መገናኘት ካሻ አጋጣሚዎችን የመጨረሱ ጉዳይ ላይ ትኩረት መስጠት ይጠበቅበታል።

የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጨዋታዎች አሸንፈው የነበረው መከላከያዎች ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ከገጠማቸው መጠነኛ የውጤት ማጣት ጉዞ ለመላቀቅ እና ዳግም ሦስት ነጥብ አሳክቶ ነጥባቸውን ከሊጉ መሪዎች ጋር ለማስተካከል የነገውን ጨዋታ ይጠባበቃሉ።

እንደ ቡድን በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ የተዋጣላቸው መከላከያዎች ይህ የተብላላው ቡድናዊ መዋቅራቸው ነገም ይጠበቃል። በተለይ ደግሞ ከኳስ ውጪ የሚኖራቸው ተግባቦታዊ የመከላከል እንቅስቃሴ ለባህር ዳሮች ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል። በሽግግሮች ላይ ግን በተለይ በቢኒያም በላይ በኩል የሚኖረው ፈጣን የማጥቃት ሀይል ኦኩቱ ኢማኑኤልን ዒላማ ከሚያደርጉት የመስመር ተሻጋሪ ኳሶች ጋር በመዳመር ግብ ለማግኛነት እንደሚጠቀማቸውም ይታሰባል።

በባህር ዳር በኩል ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ተመስገን ደረሰ አሁንም ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ቡድናቸውን ነገ አያገለግሉም። መከላከያ ደግሞ የጊዮርጊሱ ጨዋታ በቅጣት ያለፈው የመስመር ተከላካዩ ገናናው ረጋሳን በነገው ጨዋታ የሚያገኝ ይሆናል። በዚሁ ጨዋታ ተጎድቶ ተቀይሮ የወጣው አሌክስ ተሰማ የሁለት ቀን እረፍት ከተሰጠው በኋላ ወደ መደበኛ ጤንነቱ በመመለሱ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑም ተመላክቷል።

9 ሰዓት ሲል የሚጀምረውን ጨዋታ ፌዴራል ዋና ዳኛ ተካልኝ ለማ በመሐል አልቢትርነት የሚመሩት ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜያት ተገናኝተዋል። ሦስት ግቦች በድምሩ በተቆጠሩበት ግንኙነት ላይ መከላከያ አንዱን 1-0 ሲያሸንፍ ሌላኛው ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ግምታዊ አሠላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (4-1-3-2)

አቡበከር ኑሪ

አህመድ ረሺድ – ሰለሞን ወዴሳ – ፈቱዲን ጀማል – ግርማ ዲሳሳ

አለልኝ አዘነ

ፎዓድ ፈረጃ – ፍፁም ዓለሙ – አብዱልከሪም ንኪማ

ዓሊ ሱሌይማን – ኦሴ ማውሊ

መከላከያ (4-2-3-1)

ክሌመንት ቦዬ

ዳዊት ማሞ – ኢብራሂም ሁሴን – አሌክስ ተሰማ – ገናናው ረጋሳ

ኢማኑኤል ላርዬ – አለምአንተ ካሳ

ሰመረ ሀፍታይ – ቢኒያም በላይ – አዲሱ አቱላ

ኡኩቱ ኢማኑኤል