ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

የጨዋታ ሳምንቱን ስድስተኛ ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተነዋል።

ጨዋታው በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ በተለያየ የውጤት መንገድ ላይ የሚገኙ ቡድኖችን ያገናኛል። ሦስት የአቻ ውጤቶችን ብቻ ያስመዘገበው ሰበታ ከተማ የመጀመሪያ ጎሉን በሲዳማ ቡናው ጨዋታ ቢያገኝም ሙሉ ነጥብ ማሳካትን ከነገው ጨዋታ ያልማል። በሽንፈት ሊጉን የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ ሦስት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግበው ነገ በሰንጠረዡ አናት የሚያስቀምጣቸውን ውጤት ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

አምና ባዘመመበት ጊዜ ደርሰው በሚታይ መልኩ ያቀኑትን ቡድን በተቃራኒው የሚገጥሙት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የዘንድሮው ቡድናቸው የፊት መስመር ስልነት ከውጤት ያራቃቸው ይመስላል። ቡድኑ የመጨረሻ የግብ ዕድል ያገኘባቸው ቅፅበቶች ተፈጥረው ብናይም በማይታመን መልኩ ሲመክኑ በመቆየታቸው የመጀመሪያ ግቡን ለማየት እንዲዘገይ ምክንያት ሆኖታል። ይህንን ችግር የቅርፅ ለውጥ በማድረግ ወይንስ በተጨዋቾች ለውጥ ይፈቱታል የሚለው ነጥብም ከነገው ጨዋታ በፊት ለሰበታ ወሳኝ ይመስላል። ሁለተኛውን አማራጭ ከወሰዱ ግን በመጨረሻው ጨዋታው ተቀይሮ በመግባት ግቧን ያስቆጠረው ፍፁም ገብረማሪያም የተሻለው ምርጫቸው የሚሆን ይመስላል። ሦስቱን ጨዋታዎች በአራት የተለያዩ ተጫዋች ግቦች ድል ያደረገው ወላይታ ድቻ በበኩሉ ይህ ችግር ባይኖርበትም የተገኙ ዕድሎችን ወደ ግብነት የመቀየር ንፃሬው አሁንም ሊሻሻል የሚገባው በመሆኑ በነገው ጨዋታም የሚፈጥራቸው ዕድሎች ቁጥር ዝቅ ማለት አይኖርባቸውም።

ከጨዋታ ምርጫ አንፃር አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም በግልፅ እንዳስቀመጡት ወላይታ ድቻ ለውጤት ቅድሚያ የሚሰጥ በመሆኑ ከተጋጣሚው አንፃር የተቃኘ አቀራረብ ይኖረዋል። በአመዛኙ ጥንቃቄ አዘል ሆኖ ከኳስ ጀርባ መቆየትን ምርጫው ማድረጉ ሲታሰብም ተመሳሳይ ባህሪ የሚታይበት ሰበታ ከተማ ነገ ኳስ ተቆጣጥሮ ወደመጫወቱ እንዲያዘነብል የሚፈቅድ ይመስላል። ሰበታ ከተማዎች ከአጨራረስ ችግር በተጨማሪ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል የሚደርሱባቸው ስትራቴጂዎች በራሳቸው በቂ የውህደት ደረጃ ላይ የደረሰ በማይመስለው ቡድን ውስጥ አጥጋቢ አይደሉም። ከዚህ አንፃር ኳስ ተቆጣጥሮ በማስከፈት ወደ ድቻ ሳጥን የሚዘልቅባቸው መንገዶችን መፍጠሩ ላይ ሊቸገር ይችላል።

ቡድኖቹ የሚያመሳስላቸው ጠንካራ ጎን የመከላከል አደረጃጀታቸው ነው። ሁለቱም ከአራት ጨዋታዎች በሁለቱ መረባቸውን አለማስደፈራቸው ይህንን ጥንካሬ የሚያሳይ ነጥብ ነው። በመሆኑም በሁለቱም ሳጥኖች መግቢያ ላይ ብዙ የማያኩራራ የማጥቃት ሂደት ከጠጣር የመከላከል መዋቅር ጋር የሚገናኝ ይሆናል። ያም ቢሆን ወላይታ ድቻ በተለያዩ ምክንያቶች የመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ አዲስ ጥምረትን ሊተገብር የሚችል መሆኑ ለሰበታ ከተማ መልካም ዜና የሚሆንለት ይመስላል። ከዚህ በተቃራኒው ሰበታ ከተማ ደግሞ ያጣቸውን የኋላ መስመር ተጫዋቾች መልሶ ማግኘቱ ተጨማሪ ብስራት ይሆንለታል።

በነገው ጨዋታ የሰበታዎቹ ጌቱ ኃይለማርያም ከጉዳት አንተነህ ተስፋዬ ከቅጣት ሲመለሱ መሀመድ አበራ ፣ አክሊሉ ዋለልኝ እና ዱሬሳ ሹቢሳ አሁንም አላገገሙም። በተመሳሳይ ጉዳት ካለባቸው የወላይታ ድቻዎቹ ግብ ጠባቂዎች ወንድወሰን አሸናፊ እና ቢኒያም ገነቱ በተጨማሪ ደጉ ደበበም ጉዳት ሲገጥመው ከቤተሰብ ሀዘን የተመለሰው አንተነህ ጉግሳም ዘግይቶ በመድረሱ በነገው አሰላለፍ ውስጥ አይካተትም።

ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ ሀብታሙ መንግሥቴ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ባሳለፍነው ዓመት የተደረጉት የቡድኖቹ የመጀመሪያ የሊግ ግንኙነቶች በ 0-0 እና 2-2 ውጤቶች የተጠናቀቁ ነበሩ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ለዓለም ብርሀኑ

ጌቱ ኃይለማሪያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

ቢያድግልኝ ኤልያስ – ክሪዚስቶም ንታንቢ

ሳሙኤል ሳሊሶ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – ጁኒያስ ናንጄቤ

ፍፁም ገብረማርያም

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

ፅዮን መርዕድ

ያሬድ ዳዊት – በረከት ወልደዮሐንስ – መልካሙ ቦጋለ – አናጋው ባደግ

እድሪስ ሰዒድ – ንጋቱ ገብረሥላሴ – ሐብታሙ ንጉሤ

ምንይሉ ወንድሙ – ስንታየሁ መንግሥቱ – ቃልኪዳን ዘላለም