በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በቅርቡ በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የነበረውን የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከፍ አድርጎ ማንሳቱ ይታወሳል። ወደ ሴካፋ ውድድር ከማምራቱ በፊት ደግሞ በኮስታሪካ ለሚደረገው የዓለም ዋንጫ ውድድር ለመብቃት የማጣሪያ ጨዋታዎችን ማድረግ ጀምሮ ነበር። በዚህም በሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ የሩዋንዳ አቻውን በሰፋ የግብ ልዩነት በመርታት ወደ ሦስተኛ ዙር የማጣሪያው ፍልሚያ ማለፉን አረጋግጧል። የፊታችን ዓርብ ደግሞ የዚህን ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ከቦትስዋና ጋር ከሜዳው ውጪ በማድረግ ይጀምራል።
በአስራ አምስት ቀናት ልዩነት ለሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች ከሳምንት በፊት መዘጋጀት የጀመረው ቡድኑም የመጀመሪያዎቹን ቀናት በቀን 2 ጊዜ ከዛም በቀን አንድ ጊዜ ልምምዱን ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በዛሬው ዕለት የመጨረሻ ልምምዱን መስቀል ፍራኦል አካባቢ በሚገኘው 35 ሜዳ ሰርቷል።
ምንም እንኳን ቡድኑ በካፍ የልህቀት ማዕከል ማረፊያውን ቢያደርግም በማዕከሉ የሚገኘው ሜዳ ለልምምድ ምቹ አለመሆኑን ተከትሎ ያለፉትን ቀናት በ35 ሜዳ ሲዘጋጅ ነበር። ዛሬ ረፋድም ከ5 ሰዓት ጀምሮ ለአንድ ሰዓት ያክል የቆየ የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል። ከልምምዱ በፊት ደግሞ የቡድኑ አባላት ለጉዞ የሚያስፈልጋቸው የኮቪድ-19 ምርመራ አከናውነው ነበር።
በዛሬው የቡድኑ የመጨረሻ ልምምድ ላይ 21 ተጫዋቾች የተገኙ ሲሆን ሁሉም በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ችለናል። ነገ ረፋድ ደግሞ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ዓርብ ለማድረግ ወደ ቦትስዋና እንደሚያቀኑ ታውቋል። ከሁለት ሰዓታት በኋላ ደግሞ የቡድኑ አሠልጣኝ ፍሬው እና አምበሏ ናርዶስ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጡ ይሆናል።