ሪፖርት | መከላከያ ባህር ዳር ላይ ድል ተቀዳጅቷል

ባህር ዳር ከተማዎች በአርባምንጭ ከተረቱበት ጨዋታ አምስት ለውጦችን አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም በግቡ መሐከል የሚሆነው አቡበከር ኑሪን በፋሲል ገብረሚካኤል፣ ኦሲ ማውሊን በአህመድ ረሺድ፣ ሠለሞን ወዴሳን በፎዐድ ፈረጃ፣ ሳላምላክ ተገኘን በመናፍ ዐወል እንዲሁም ዜናው ፈረደን በዓሊ ሱሌይማን ተክተዋል። መከላከያዎች በበኩላቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ጎል አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ ገናናው ረጋሳን እና ሰመረ ሀፍታይን ብቻ በብሩክ ሰሙ እና አለምአንተ ካሳ ቦታ አሰልፈው ጨዋታውን ለመጀመር ሜዳ ተገኝተዋል።

በሁለት የተለያየ የአጨዋወት መንገድ ሲጫወቱ የታዩት ባህር ዳር እና መከላከያ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች እምብዛም ለግብ የቀረበ ጥቃት ሲሰናዘሩ አልነበረም። እርግጥ ጨዋታው እንደተጀመረ ኦኩቱ ኢማኑኤል እና ቢኒያም በላይ በጊዜ የፋሲልን መረብ ለማግኘት ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ከኳስ ጋር ረዘም ያለ ጊዜ ማሳለፍ የፈለጉት ባህር ዳሮች ደግሞ በ9ኛው ደቂቃ ግሩም ሀጎስ አህመድ ረሺድ ላይ ጥፋት ሰርቶ የተገኘውን የቅጣት ምት በፍፁም አማካኝነት ወደ ግብ ልከውት ቀዳሚ ለመሆን ሞክረዋል።

የመጀመሪያውን የቡድኑን ሙከራ ከቅጣት ምት ያደረገው ፍፁም በ21ኛው ደቂቃ ደግሞ ረዘም ካለ የኳስ ቅብብል በኋላ ለግርማ ዲሳሳ አቀብሎት ዳግም የተረከበውን ኳስ ከወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ ወደ ግብ መትቶት ነበር። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ዒሊ ሱሌይማን ሳጥን ውስጥ የደረሰውም ጥሩ ኳስ ለመጠቀም ሲጥር ተረባርበው የመከላከያ ተጫዋች ኳሱን ወደ ውጪ አውጥተውታል። በተከላካዮች ተመቶ የወጣውን ኳስ ከርቀት ያገኘው አለልኝ አዘነ ደግሞ ኳሱን መሬት ለመሬት ወደ ግብ ቢልከውም ክሌመንት ቦዬ እምብዛም ሳይቸገር ተቆጣጥሮታል።

በተቃራኒው ቀጥተኛ አጨዋወታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት መከላከያዎች በ26ኛው ደቂቃ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህም አዲሱ አቱላ ከመሐል የላከውን ኳስ ሰመረ ሀፍታይ ዐየር ላይ በመዝለል በግንባሩ ግብ ላይ ለማሳረፍ ቢመታውም ፋሲል ገብረሚካኤል ይዞበታል። መከላከያዎች ይህንን ጥቃት ፈፅመው ቢመለሱም ከደቂቃ በኋላ ተመሪ የሚሆኑበት ጎል ተቆጥሮባቸው ነበር። ከውሃ እረፍት የቆመው ጨዋታ ሲቀጥል የመዓዘን ምት ያገኙት ባህር ዳሮች ኳሱን መሬት ለመሬት ሲያሻሙት ተከላካዩ አሌክስ ተሰማ በሚገባ ሳያፀዳው ቀርተው ፈቱዲን ጀማል እንደምንም ተንሸራቶ ለመጠቀም ሞክሮ ነበር። ነገርግን ፈቱዲን የኳሷን አቅጣጫ ወደ ግብ ለማስቀየር ያደረገው ጥረት ብዙም ሀይል ስላልነበረው የግብ ዘቡ ክሌመንት በጥሩ ቅልጥፍና ደርሶ አድኖበታል። ቀጣዮቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ግን አንድም ለግብ የቀረበ ሁነት ሳያስተናግዱ የፉክክር ደረጃቸው ወረድ ብሎ ታይቷል።

በአንፃራዊነት ፍጥነቱ ጨመር ብሎ የጀመረው የሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ የግብ ማግባት ዕድሎች ተፈጥረውበታል። በቅድሚያ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለውጠው የገቡት መከላከያዎች በ49ኛው እና በ55ኛው ደቂቃ የቅጣት ምትን መነሻ ባደረገ ኳስ ግብ ሊያገኙ ነበር። በተለይ በ55ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ዓለምአንተ ካሳ ያሻገረውን ኳስ ሰመረ በግንባሩ በመግጨት መረብ ላይ ሊያዋህደው የነበረ ቢሆንም ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወቷል። በሁለቱ የመከላከያ ሙከራዎች መሐል ደግሞ የባህር ዳሩ የአጥቂ አማካይ ፍፁም ከርቀት ጥሩ ኳስ መትቶ ክሌመንት ወደ ውጪ አውጥቶበታል።

እጅግ ተሻሽለው ይህኛውን አጋማሽ የቀረቡት መከላከያዎች በ60ኛው ደቂቃም ሌላ ለግብ የቀረቡበት ሁነት ተፈጥሮ ነበር። አጋማሹ ሲጀምር ግሩም ሀጎስን ለውጦ ወደ ሜዳ የገባው ብሩክ ሰሙ የባህር ዳር ተከላካዮችን ስህተት ተከትሎ ያገኘውን ኳስ እየገፋ ሳጥን ውስጥ በመግባት ወደ ግብ መቶት ነበር። ነገርግን ፋሲል ገብረሚካኤል በጥሩ ብቃት ኳሱን ወደ ውጪ አውጥቶበታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ግን መከላከያዎች የልፋታቸውን ፍሬ አግኝተዋል። በዚህም ኳስ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ሲሻገር የመሐል ተከላካዩ መናፍ ዐወል በእጁ ነክቶ የፍፁም ቅጣት ምት ተገኝቷል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ቢኒያም በላይ አስቆጥሮታል። እርግጥ ቢኒያም የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ፋሲል ቢያድንበትም የግብ ዘቡ ኳሱ ሳይመታ ከመስመሩ እግሩን በማንሳቱ ፍፁም ቅጣት ምቱ ተደግሞ ቢኒያም ሁለተኛ ዕድል አግኝቶ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ባህር ዳር ከተማዎች ዳግም ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተፋዘዘው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለማስተካከል ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ይባሱኑ በ85ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረው ቢኒያም የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ተከላካዮችን በአስደናቂ ሁኔታ በማለፍ በቀኝ እግሩ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታውም በመከላከያ ሁለት ለምንም አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ሦስት ነጥብ ያሳካው መከላከያ ከመሪው ፋሲል እኩል ነጥቡን 10 በማድረስ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል። የዛሬውን ጨምሮ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ባህር ዳር ደግሞ ወደ 6ኛ (በ7 ነጥብ) ደረጃ ሸርተት ብሏል።