ከዛሬው ቀዳሚ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኖች ከሱፐር ስፖርት ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።
አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ
ስለጨዋታው
ሙሉ ለሙሉ በተዘጋጀንበት መንገድ ነው ስናካሂድ የነበረው። ተጋጣሚያችን ወደ ኋላ አፈግፍጎ ዘግቶ ነበር የሚጫወተው። እንደዛም ሆኖ በፍፁም ቅጣት ምት እና በተከላካዮቻችን ትኩረት ማነስ ምክንያት ውጤቱን አጥተናል። መከላከያዎች በመረጡት አጨዋወት ውጤት ይዘው ወጥተዋል። በዚህ አጋጣሚ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለው።
በሁለተኛው አጋማሽ ተጋጣሚ ስለመረጠው አጨዋወት
በሁለተኛው አጋማሽ የተጨዋች ቁጥር ጨምረው እኛ እንዳንመሰርት ያደርጉ ነበር። ነገር ግን ግቡን ሲያስቆጥሩ የዛ መንስኤ ነው ማለት አልችልም። እኛ በመረጥነው መንገድ መስርተን ለመጫወት ብዙ ጥረናል። ነገር ግን ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ስንገባ የቅንጅት እና የአጨራረስ ችግራችንን የግድ ማስተካከል አለብን ብዬ ነው የማስበው። በተረፈ ግን በጨዋታው እና ተጫዋቾች ባሳዩት ጥረት ደስተኛ ነኝ።
ቡድኑ የጨዋታ መንገዱን ስለማግኘቱ
አግኝተናል ብዬ ነው የማስበው ፤ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከውጤቱ አለመስተካከል በስተቀር የምንፈልገውን ነገር እያደረግን ነው። ቡድኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ አለው። አልፎ አልፎ ግን በጉዳት እንደ ማዉሊ ዓይነት ተጫዋቾች ስናጣ ወይንም ከጉዳት የተመለሱ የዓሊ ዓይነት ተጫዋቾች ስናገኝ ደግሞ መቶ ፐርሰንት ከፊት የምትፈልገውን ነገር አናገኝም። ይሄ እየተስተካከለ ሲሄድ ቡድኑ የጀመረውን ነገር ያስቀጥላል ብዬ አስባለሁ።
በሽንፈቶቹ ውስጥ መስተካከል ስላለበት ነገር
ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ስንደርስ ያሉትን መቻኮሎች እና አለመረጋጋት እንዲሁም ያገኘናቸውን ዕድሎች መጠቀም በሁለቱ ጨዋታዎች ማስተካከል ያለብን ይመስለኛል።
አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – መከላከያ
ቡድኑ በታሰበው መንገድ ስለመጫወቱ
ከዕረፍት በፊት ብዙ ስህተቶችን ፈፅመናል። በስልት ደረጃ ማድረግ የሚግባንን አላደረግንም። ከዕረፍት በኋላ ግን ያንን ተግብረናል። ምክንያቱም እንዳየነው ከሆነ ባህር ዳር ከኋላ ብዙ ስህተቶችን የሚሰራ ቡድን ስለሆነ በዛ ነበር የሰራነው። ከዕረፍት በፊት ስለተጣደፉ ከፍተቶች ስለነበሩ ትክክል አልነበርንም። ከዕረፍት በኋላ ግን የተባባልነውን ነገር አርመን በመግባታችን ተጫዋቾችም በመቀየራችን በሚሰሩት ስህተቶች ለማሸነፍ ችለናል።
ግብ ስለማስቆጠር ችግር
በክንፍ የምናጫውታቸው ተጫዋቾች ጋር ጉጉት ስላለ የልምድ ጉዳይ ነው። ልምድ ደግሞ በመጫወት የሚመጣ ነው። ይደርሳሉ መጨረስ ላይ ችግር አለብን። እነሱ ከልምድ ጋር የሚመጡ ናቸው። ስለዚህ ያንን ካስተካከልን የተሻሉ ጎሎችን ማስቆጠር እንችላለን።
ስለቢኒያም በላይ ብቃት
ቢኒያም ከኳስ ጋር በሚሰራቸው ሥራዎች ሳይሆን ሙሉ ኃላፊነት ከመሀል ሜዳ ላይ ያለውን እንዲመራ ከኋላ ያለውን ለአሌክስ እንደሰጠን ሁሉ ሰጥተነዋል። ቢኒያምን ስናጣ ብዙ ነገር ነው የምናጣው ፤ በኳስ የሚሰራውን ሥራ ልምድ ፣ ያለኳስ የሚሰራውን ሥራ ልምድ። ስለዚህ ጎሎችን ከማስቆጠር በተጨማሪ ቡድኑን የመምራት አቅሙ ለእኛ ይጠቅመናል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጎላ ባለ ድምፅ ቡድናቸውን ስለመምራታቸው
ከአዲስ አበባ ጋር በጣልነው ነጥብ እስካሁን ቁጭት አለ። የጣልነውም በመዘናጋት ነው። እውነት ለመናገር ዛሬም ከዕረፍት በፊት ተዘናግተን ነበር። እኛ ብዙ ዕድል አላገኘንም። በብዛት ሰብረውም ባይገቡ ኳስ ለመቆጣጠር በእኛ ሜዳ ላይ ነው የዋሉት። ያ የመዘናጋት ነው። ስለዚህ ያ ዋጋ እንዳያስከፍለን ስለተነጋገርን አንዳንዴ ጊዜ ማነቃቃት ይኖርብሀል። ያንን ለማድረግ የሥራውም ፀባይ ስለሆነ መጮህ አለብህ።