ኢትዮጵያ ቡና ታፈሰ ሰለሞን ላይ ቅጣት ሲያስተላልፍ ተጫዋቹ ውሳኔውን ተቃውሟል

መገኘት በሚገባው የልምምድ ቦታ አለመገኘቱን በመግለፅ ኢትዮጵያ ቡና ታፈሰ ሰለሞን ላይ ቅጣት ማስተላለፉ ታውቋል።

በትናንትናው ምሽት ዘገባችን ታፈሰ ሰለሞን ልምምድ አለመገኘቱን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ለክለቡ ፅህፈት ቤት ሪፖርት እንዲያደርግ መደረጉን ገልፀን ስለሁኔታውም ታፈሰ ህመም አጋጥሞት ልምምድ ላይ አለመገኘቱን እና በአንፃሩ ክለቡ የዲሲፕሊን ውሳኔ ሊወሰንበት እንደሚችል ገልፀን ነበር።

ዛሬ ማለዳ ላይ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እና ተጫዋች ታፈሰ ሰለሞን በጉዳዩ ዙርያ በክለቡ ቢሮ እንደተነጋገሩ እና ውሳኔው ከሰዓት እንደሚደርሰው ተነጋግረው ተለያይተዋል።

ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ታፈሰ ሰለሞን የክለቡ ቡድን መሪ በደረሰው መረጃ መሰረት ከአንድ ወር በላይ ደሞዙ እንዳይከፈለው መወሰኑን አውቀናል። ሆኖም ታፈሰ ውሳኔውን እንደማይቀበልና በክለቡ ካልተፈለገ በስምምነት መለያየት እንደሚፈልግ ገልፆ ደብዳቤውን ሳይቀበል ከቢሮ መውጣቱን ተጫዋቹ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፇል።

ያጋሩ