ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና

የአምስተኛውን ሳምንት የመዝጊያ ዕለት ቀዳሚ ጨዋታ በዳሰሳችን ቃኝተነዋል።

ከወገብ በታች ባለው የሰንጠረዡ ክፍል ለተቀመጡት ሁለቱ ቡድኖች የነገው ጨዋታ አሸናፊውን ወደ መሪዎቹ የማስጠጋት አጋጣሚን ይዞ የሚመጣ ነው። በውጤት ረገድ ሁለቱን ቡድኖች የሚያመሳስላቸው በአንድ ጨዋታ ላይ በተጋጣሚያቸው ላይ ባሳዩት የበላይነት ነው። ሁለተኛው ሳምንት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን ሲዳማ ቡና ደግሞ ድሬዳዋ ከተማን ሲረቱ ያሳዩት አቋም የእስካሁኑ ከፍታቸው ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን ነገሮች እንደጠበቁት አልሄደላቸውም። ጊዮርጊሶች ከሁለት የአቻ ውጤቶች በላይ ማስመዝገብ ሲሳናቸው ሲዳማዎች ሽንፈትና ነጥብ መጋራት የቀጣይ ጨዋታዎቻቸው ውጤቶች ነበሩ። በመሆኑም ተጋጣሚዎቹ የድል መንገዱን መልሰው ለማግኘት የሚፋጠጡበት ጨዋታ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት እጅግ ተዳክሞ የታየው የቡድኖቹ ጎን በማጥቃት ረገድ ያላቸው አካሄድ ነው። በእነዚህ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስመዘገበው ቅዱስ ጊዮርጊስ በፊት መስመር ተሰላፊው ላይ የተማመነ አይመስልም። በቦታው ኢስማኤል ኦሮ አጎሮን እና ቦታ ቀይሮ የተሰለፈው አማኑኤል ገብረሚካኤልን ቢጠቀምም በፈለገው መጠን የፊት መስመሩን ስል ማድረግ አልቻለም። ከዚህ ባለፈ ቡድኑ የሚያጠቃበት መንገድ አልፎ አልፎ ቀጥተኝነት ይታይበት እንጂ ጥርት ያለ መልክ አልያዘም። ኳስ መስርቶ ለመውጣት የሚያደርገውም ጥረት ዝቅ ያለ በመሆኑ ተጋጣሚዎች እንዲደራጁ ጊዜ ሲሰጥ ይታያል። ይህም በመሆኑ ይመስላል ከመስመር የሚነሱ አጥቂዎቹ አስፈሪነትም ቡድኑ ኳስን ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ከሚያደርስበት መንገድ ጋር የተጣጣመ አይመስልም።

በሲዳማ ቡና በኩልም ያለው እውነታ ከዚህ እምብዛም የራቀ አይደለም። በእርግጥ ፊት ላይ ቡድኑ በይገዙ ቦጋለ መፅናቱ እና ወጥነት ያለው የማጥቃት ዕቅዱ የተሻለ ቅርፅ ኖሮት እንዲታይ አድርገውታል። ነገር ግን በመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት ተሳትፎ ላይ የተመሰረተው ጠንካራ ጎኑ በተጋጣሚዎች ዓይን ውስጥ ከገባ ወዲህ ሌሎች አማራጬቹ ውጤታማ አልሆኑም። ሁኔታው ፍሬው ሰለሞንን ብቸኛ የፈጠራ ምንጭ አድርጎት ሲታይ የእሱን ኃላፊነት ለዳዊት ተፈራ ለማጋራት የተሞከረበት መንገድም በመጨረሻው ጨዋታ ላይ ውጤት ሳያመጣ ቀርታቷል።

በመከላከሉ ረገድ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ መረጋጋት ይታይበታል። ሆኖም በመከላከያው ጨዋታ በመልሶ ማጥቃት ሲቸገር መታየቱ የሲዳማ ቡናዎች የጨዋታ ዕቅድ መነሻ ከሆነ ውጤታማ ሊያደርጋቸው ይችላል። በተጨዋች ጉዳት አስገዳጅ ለውጥ የሚደረግበት የሲዳማ ቡና የኋላ መስመርም እንዲሁ በሰበታው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ የታየበት ክፍተት ከተደገመ ከእይታ ውጪ ሳጥን ውስጥ የሚደርሱ እንደ ሀይደር ሸረፋ ዓይነት አማካዮች የግብ ዕድሎችን ሊያገኙ ይችላሉ።

ሁለቱ ቡድኖች በደካማ የማጥቃት መንገዶች ከመመሳሰላቸው ባለፈ በቡድናቸው ውስጥ ያለው የሥነ ልቦና ሁኔታም ሊፈትናቸው ይችላል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች የሚታይባቸው የድል ርሀብ እና በሁለቱም አጋማሾች በማይዛነፍ ታጋት እና ትኩረት የመጫወት ችግር ውጤት ያልያዙበት ሌላኛው ምክንያት ነው ማለት ይቻላል። ሲዳማ ቡናዎችም በመቀመጫ ከተማቸው ጨዋታዎችን እንደማድረጋቸው የውጤታቸው እንደተጠበቀው አለመሆን ከደጋፊው በኩል የሚመጣውን ጫና ከፍ እያደረጋባቸው ይገኛል። ከታክቲካዊ ጉዳዮች በዘለለ እነዚህን እክሎች በብቃት መቋቋም የሚችለው ቡድን በተሻለ ተነሳሽነት ጨዋታውን አሸንፎ የመውጣት ዕድል እንዳለው ይገመታል።

በጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ ግደይን ሲዳማ ቡና ደግሞ ጊትጋት ጉትን በጉዳት ያጣሉ።

ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 22 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 14 ጊዜ በማሸነፍ ሰፊ የበላይነት ያለው ሲሆን ሲዳማ ቡና ሁለት ጊዜ ብቻ አሸንፏል። በቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል።

– በግንኙነቶቹም ቅዱስ ጊዮርጊስ 30 ኳሶችን ከመረብ ሲያሳርፍ ሲዳማ ቡና ደግሞ 10 ጎል አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ቻርለስ ሉኩዋጎ

ሄኖክ አዱኛ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ቸርነት ጉግሳ

ሀይደር ሸረፋ – በረከት ወልዴ

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ከነዓን ማርክነህ – ቡልቻ ሹራ

ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ

ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

ተክለማሪያም ሻንቆ

አማኑኤል እንዳለ – ግርማ በቀለ – ያኩቡ መሀመድ – ሰለሞን ሀብቴ

ብርሀኑ አሻሞ – ቴዎድሮስ ታፈሰ

ዳዊት ተፈራ – ፍሬው ሰለሞን – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ይገዙ ቦጋለ

ያጋሩ