ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ጅማ አባጅፋር

እስካሁን ድል ያላደረጉ ሁለት ክለቦች የሚያደርጉትን የአምስተኛ ሳምንት የማሳረጊያ ጨዋታ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

ዓምና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና ከአስከፊው የዘንድሮ አጀማመር ወጥቶ ወደ ጠንካራነቱ ለመምጣት የሚንደረደርበትን አዎንታዊ ውጤት ነገ ለማስመዝገብ እንደሚጥር ይገመታል።

በብዙ መስፈርቶች የወረደ ብቃት እያሳየ የሚገኘው ክለቡ አሁን ከሚገኝበት የወራጅ ቀጠና ለመውጣት ጨዋታዎችን ማሸነፍ የግድ ይለዋል። ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ደግሞ ግቦችን ማስቆጠር ይጠበቅበታል። እስካሁን በታዩት አራት ጨዋታዎች ግን ቡድኑ የምን ጊዜውም የአንድ የውድድር ዘመን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች (አቡበከር ናስር) ይዞ ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆኖ ታይቷል። በተለይ መሐል ለመሐልም ሆነ በሁለቱ መስመሮች የሚደረጉት የቡድኑ ፍጥነት የተሞላባቸው የማጥቃት እንቅስቃሴዎች መቀነሳቸው ደግሞ ለዚህ ምክንያት ይመስላል። ከዚህ ውጪ አቡበከር በአሠልጣኙ የሚሰጠው የመጫወቻ ቦታም ለክፍተቱ እንደ ምክንያትነት የሚያቀርቡት አልጠፉም። የሆነው ሆኖ ግን ካሳዬ አራጌ በአራቱ ጨዋታዎች የተቀዛቀዘው የማጥቃት አጨዋወታቸው ነገ ካላረሙ አሁንም የጎል ድርቅ እንደሚያገኛቸው ይታሰባል።

ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ የታመመው በማጥቃቱ ብቻ አይደለም ፤ በመከላከሉም ጭምር። እርግጥ ቡና በመከላከሉ ረገድ ዓምናም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳሉበት ቢታወስም የዘንድሮው ግን ትንሽ ከበድ ያለ ይመስላል። በተለይ ቡድኑ ኳስ ሲያጣ በቶሎ ክፍተቶችን የመዝጋት እና ኳስን በፍጥነት ከተጋጣሚ የመቀማት ችግር እንዳለበት ተስተውሏል። ይህ ከኳስ ውጪ የሚደረግ እንቅስሳሴ ደግሞ ነገም ላላ ብሎ ከታየ እንደ ቡና ሦስት ነጥብ ናፍቆት የሚመጣው ጅማ አባጅፋር ሊጠቀምበት ይችላል።

እንደ ኢትዮጵያ ቡና ሁሉ እስካሁን ሦስት ነጥብ ከተጋጣሚ መውሰድ ያልቻለው ጅማ አባጅፋርም ከድል ጋር በመታረቅ የደረጃ ሰንጠረዡን ግርጌ ለመላቀቅ ነገ ጠንክሮ ጨዋታውን እንደሚቀርብ ይታመናል።

አዲስ አሠልጣኝ ከመቅጠር ጀምሮ በርካታ አዳዲስ ፊቶችን ለክለቡ በማስተዋወቅ የውድድር ዓመቱን የጀመረው ጅማ አባጅፋር ባለፉት አራት ጨዋታዎች በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ የቅንጅት ችግር ታይቶበታል። ለዛም ይመስላል አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ በየጨዋታው የተጫዋች አደራደር ቅርፅ እና ከሁለት በላይ ተጫዋቾችን እየቀያየሩ ጨዋታዎችን ሲቀርቡ የሚታየው። ምንም ቢሆን ግን ፈጣኖቹ አጥቂዎች ዳዊት ፍቃዱ እና መሐመድኑር ናስር በሽግግሮች ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ ምናልባት ነገ ለቡና ፈተና ሊሆን ይችላል። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ወደ መሐል ሜዳ ተጠግተው የመጫወት ዝንባሌ በአመዛኙ ስለሚያዘወትሩ ፈጣኖቹ አጥቂዎች ከተከላካዮቹ ጀርባ የሚገኘውን ቦታ ለመጠቀም እንደሚታትሩ ይገመታል።

በሊጉ ዝቅተኛ ግብ ተጋጣሚ ላይ በማስቆጠር (1) እንዲሁም በተቃራኒው ብዙ ግቦችን በማስተናገድ (9) ቀዳሚው ክለብ የሆነው ጅማ ገና በጊዜ የሰበሰበውን የግብ እዳ ለማቃለል የማጥቃት እንቅስቃሴውን ማስተካከል እንዳለበት ሁሉ በየጨዋታው ክፍተቶቹ ብዙ የሆኑትን የኋላ መስመሩንም መላ ማለት ይገባዋል። ከግብ ጠባቂ ጀምሮም በተከላካዮቹ ላይ የሚታየውን መቀያየርም እርጋታን እና መናበብን ለሚሻው መስመር ፈተና ይመስላል። በነገው ጨዋታም በመስመሩ ላይ በድሬው ጨዋታ የታዩት ያለመረጋጋት፣ የልምድ ማጣት እና ያለመናበብ ክፍተቶች መታረም ይጠበቅባቸዋል።

ይህንን ጨዋታ ፌዴራል ዋና ዳኛ ተስፋዬ ግሩሙ በአልቢትርነት የሚመሩት ይሆናል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለስድስት ጊዜያት ተገናኝተው ሁለት ሁለት ጊዜ ሲሸናነፉ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። አምስት አምስት ጎሎችም አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

ኃይሌገብረትንሳኤ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አስራት ቱንጆ

አቤል እንዳለ – አማኑኤል ዮሐንስ – ዊልያም ሰለሞን

አላዛር ሺመልስ – እንዳለ ደባልቄ – አቡበከር ናስር

ጅማ አባጅፋር (4-2-3-1)

ዮሐንስ በዛብህ

ሽመልስ ተገኝ – በላይ አባይነህ – ያብስራ ሙሉጌታ – ኢዳላሚን ናስር

ሙሴ ከበላ – ሮጀር ማላ

ዱላ ሙላቱ – መስዑድ መሐመድ – መሐመድ ኑርናስር

ዳዊት ፍቃዱ